የሥልጠና ዝርዝር
2.3. መደበኛ ገለጻ - የመድልዎ አልባነት መርሆ
የዚህ በሰብአዊ መብቶች ላይ የተመሠረተ አቀራረብ ቁልፍ ፍሬ ነገር የመድልዎ አልባነት ሕጎችና ፖሊሲዎች መጽደቅ እንደ ሆነ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ አካል ጉዳተኞች እኩል ሰብአዊ ፍጡራን መሆናቸውንና በዚህም፣ በተለይ የሥራ ስምሪትን አስመልክቶ፣ እኩል አያያዝና እኩል ዕድሎች የማግኘት መብት አላቸው፡፡ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ ውስጥ አቋራጭ መርሆ የሆነውን መድልዎ አልባ መርሆ ለመግለጽ
የገለጻ ማሳያ 14 ይጠቀሙ፡፡ መርሁ የተመድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ድንጋጌን ጨምሮ ዋነኛ በሆኑት በሁሉም የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ውስጥ ይገኛል፡፡ በአካል ጉዳት ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸም መድልዎን የድንጋጌው አንቀጽ 2 «በፖለቲካዊ፣ በኤኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ በባህላዊ፣ በሲቪል ወይም በማንኛውም ሌላ መስክ የሁሉንም ሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች እውቅና፣ ተጠቃሚነትና በሥራ ላይ መዋል የመጉዳት ወይም ዋጋ የማሳጣት ዓላማ ወይም ውጤት ያለው ማንኛውም ልዩነት፣ ማግለል ወይም ገደብ» በማለት ያብራራዋል፡፡ ይህም «ተመጣጣኝ ማመቻቸት» መነፈግን ጨምሮ ሁሉንም የመድልዎ ዓይነቶች ያካትታል፡፡ የድንጋጌው አንቀጽ 5 «የአካል ጉዳተኞችን ተጨባጭ እኩልነት ለማፋጠን ወይም ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ ልዩ እርምጃዎች በዚህ ድንጋጌ ስምምነቶች መሠረት እንደ መድልዎ» እንደማይታዩ እውቅና በመስጠት በመድልዎ አልባነት መርሆ ዙሪያ ዝርዝር ያትታል፡፡ በእርግጥ በአዎንታዊ እርምጃ እኩልነትን ለማሳደግ የታሰቡ ከሆነ በአንድ ሥራ እርግጠኛና ትክክለኛ ፍላጎቶች ላይ በሚመሠረቱበት ጊዜ የሥራ ስምሪት አሠራሮች አድላዊ እንደ ሆኑ አይቆጠሩም፡፡
በአሁኑ ጊዜ መድልዎን የሚከለክል ሕግ ለሥራ ስምሪት እንደ መሠረታዊ ነገር ተቆጥሮአል (የገለጻ ማሳያ 15)፡፡ የመድልዎ አልባነት ሕግ ዓላማ በአካል ጉዳት፣ እንዲሁም በሌሎች ጭብጦች፣ ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸም መድልዎን መከልከል ነው፡፡ ቁጥራቸው በዛ ያሉ መንግሥታት በጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ ለሚገኙ ልዩ ቡድኖች በሚገያለግሉ ሕጎች፣ ወይም አካል ጉዳት ነክ በሆኑ ሕጎች፣ አማካይነት በአካል ጉዳት ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸም መድልዎን ይከለክላሉ፡፡ ይህ በሚመለከታቸው ሁኔታዎች የተረጋገጠ በማይሆንበት ቦታ አካል ጉዳተኞችን ለማግለልና እኩል የሥራ ስምሪት ዕድሎችን ለመንፈግ አካል ጉዳት እንደ ምክንያት እንደሚያገለግል ያደገ እውቅና ማግኘቱን ያንጸባርቃል፡፡ እንዲህ ያሉት ሕጎች ዓላማ የአካል ጉዳተኞችን መገለልና እንደ አካል ጉዳት ባሉ ልዩ መታወቂያዎች ምክንያት የሚደረግ የእኩል ዕድሎች መነፈግን ለመዋጋት ነው፡፡ አካል ጉዳትን ጥበቃ ያገኘ ጭብጥ በማድረግ ሕጉ በአድላዊ ባህርይ ላይ ጥበቃ የሚዘረጋ ሲሆን መድልዎ አልባ ደንቡን የሚጥሱትን ሰዎች ይቀጣል፡፡
- የአካል ጉዳት መድልዎ አልባ ሕግና ፖሊሲዎች ሊወስዱ የሚችሉአቸውን የተለያዩ መልኮችና ትኩረቶች ለተሳታፊዎች ለማስረዳት የገለጻ ማሳያ 16ን ይጠቀሙ፡፡ አንድ ሕግ ወይም ፖሊሲ አካል ጉዳተኞችን እኩል ካልሆነ አያያዝ መጠበቅ የሚችልባቸውን ለአገር ውስጥ አግባብነት ያላቸውን አንዳንድ ተጨማሪ መስኮች እንዲፈጠሩ ተሳታፊዎችን ይጠይቁ፤ እንዲሁም የተሰጡትን ምሳሌዎች እንዲጽፉ ያድርጉ፡፡
- በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈጸመው መድልዎ እንደ ሥርዓተ ፆታ፣ ጐሣዊ ማንነት፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ያሉ መድልዎ ከተከለከለባቸው አንዳንድ ጭብጦች አንዱ መሆን እንደሚችል ለማሳየት የገለጻ ማሳያ 17ን ይጠቀሙ፡፡ የተጠበቀ ሁኔታ በሕግ የተረጋገጠባቸው አንዳንድ ለአካባቢው አግባብነት ያላቸውን መስኮች እንዲያመነጩ ተሳታፊዎችን ይጠይቁ፤ መልሶቻቸውንም በተገላጭ ወረቀቱ ላይ ይመዝግቡ፡፡
- ደግሞም የመድልዎ አልባ ሕግን ግንዛቤ ከፍ ማድረግን ለመርዳትና እንዲሁም በአካል ጉዳተኞችና አካል ጉዳት በሌለባቸው ሰዎች መካከል መኖር ስላለበት እኩል አያያዝ ደንቦችን መያዝ እንዴት እንደሚችል ለማስረዳት የገለጻ ማሳያ 17ን ይጠቀሙ፡፡ በገለጻ ጽሁፉ የተሰጡትን ምሳሌዎች አጉልተው ያሳዩ፡፡