የሥልጠና ዝርዝር

2.2. መደበኛ ገለጻ አካል ጉዳት እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ

  • ባለፈው ክፍለ ዘመን አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች በሚታዩበት፣ ከእነርሱ ጋር ባለው ግንኙነት፣ በሚያዙበትና ለእነርሱ ድጋፍ በሚደረግበት መንገድ ዋነኛ አዝጋሚ ልውጥ ማየታችንን ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ለብዙ ክፍላተ ዘመናት (ከባህላዊ አጉል እምነቶች ጋር በተያያዘ ሁኔታ) አካል ጉዳት መፈራት ያለበት ወይም ሊታዘንለት የሚገባ ነገር ነው፣ አካል ጉዳት በህክምናና በተሀድሶ አያያዝ፣ አዘውትሮ በተገለሉ ማእከሎች ውስጥ እስከ ተወሰነ ደረጃ በባለሙያ ሊስተካከል የሚችል ነገር ነው በሚሉ አስተሳሰቦች ላይ ተመሥርቶ ብዙ አካል ጉዳተኞች ከአካታቹ ኅበረተሰብ ተገልለው ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ የአካል ጉዳት ግንዛቤ መንገዶች ጋር የሚገናኘው የፖሊሲ ትኩረት በመጀመሪያ ጉዳይ በምጽዋት፣ በሁለተኛ ጉዳይ ደግሞ የህክምናና ተያያዥ የተሀድሶ ፍላጎቶቻቸውን - አንዲሁም የደህንነትና ማኅበራዊ ዋስትና አሰጣጦችን - በሚያስተናግዱ አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይ ነበር፡፡ እነዚህ አቀራረቦች በአጠቃላይ የአካል ጉዳት የምጽዋት ሞዴልና የህክምና ሞዴል በመባል የሚታወቁ ሲሆን ወደ አካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ መገለል አምርተዋል፡፡

    በቅርብ ዓመታት በኅብረተሰብ ውስጥ በአጠቃላይ በሥራ ዓለም የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በሚገቱ ማኅበራዊና ተፈጥሮአዊ የአካባቢ ጭብጦች ላይ ይበልጥ እያደገ የሚሄድ አጽንኦት አለ፡፡ ይህ አዝማሚያ የአካል ጉዳተኞችን መብቶችና እንደ ዜጎች ያላቸውን ቦታ በላቀ ሁኔታ ወደ ማወቅ አምርቶአል፡፡ የዚህ መነሻ የሆነው አካል ጉዳትን በመገንዘብ ረገድ የተገኘው ለውጥ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደ ግል ችግር ወይም አደጋ ከመታየት ይልቅ ብዙዎቹ የተሳትፎ መሰናክሎች ሰዎች ስለ አካል ጉዳት ከሚያስቡበትና ከሚፈጥሩአቸው የተዛቡ ግምቶች ጋር ተዳብሎ ኅብረተሰብ ከተገነባበት ወይም ከተደራጀበት መንገድ እንደሚነሡ እውቅና አለ፡፡ አዝጋሚ ለውጡ በፖሊሲ ሁኔታዎች ከህክምና ሞደል ወደ ማኅበራዊ ሞዴል - ወይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚታወቅበት በመብቶች ላይ ወደ ተመሠረተ ሞዴል - በመሸጋገሩ ይበልጥ አጠቃላይ የሆነ የአካል ጉዳት ተቀባይነት አለ፡፡ በውጤቱም አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች በኅብረተሰብ ውስጥ እንደ አምራች ዜጎች የሚጫወቱትን ሚና ለመሙላት እጅግ የበለጠ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ይህ ለውጥ በሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች

    ከጅምር እስከ ፍጻሜ በዘዴ ለማጥራት እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በኅብረተሰብ ውስጥ ወደ ዳር ተገፍተውበት ከነበረው አካል ጉዳትን እንደ ማኅበራዊ ደህንነት ጉዳይ የመቁጠር የአገልግሎቶች አመለካከት ለመለወጥ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶአል፡፡
    የገለጻ ማሳያ 9ን iተጠቅመው ማኅበራዊው ሞዴል ለሙሉ ተሳትፎ እንቅፋት የሆኑትን አካባቢያዊ መሰናክሎችን በመበጣጠስ ላይ ሲያተኩር የህክምናው ሞዴል ግን «ስህተት እንዳለበት የሚታሰበውን ነገር በመጠገን» ላይ የተመሠረተ መሆኑን በመግለጽ በህክምናና በማኀበራዊ ሞዴሎች መካከል ያለውን ልዩነት ያስረዱ፡፡

    የህክምናው ሞዴል የግለሰቡን እክል፣ አካል ጉዳትና ውሱንነቶች ያጋንናል፡፡ ለማንኛውም ሰው አንድ ደንብ አለ በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ላይ ተመሥርቶ «ትክክለኛ» ነው ተብሎ በሚታሰበው መሠረት ግለሰቡን መልሶ ለመጠገን ይሻል፡፡ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኛው ግለሰብ በሚመርጠው መንገድ ሳይሆን በአጠቃላይ አለ በሚባለው ላይ ተመሥርተው ይሰጣሉ፡፡

    ማኅበራዊው ሞዴል አካል ጉዳተኞችን በአገልግሎቶችና በሚፈልጉት ድጋፍ መካከለኛ ክፍል ማስቀመጥ የሚሻ ሲሆን በአቅም ላይ አጽንኦት ያደርጋል - ማድረግ በማይችሉት ተቃራኒ ግለሰቡ ማድረግ የሚችለው ነገር ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ማኅበራዊው ሞዴል ባህርይ በአካባቢ ተጽእኖ እንደሚደረግበት ሲገልጽ ለምሳሌ የዊልቼር ተጠቃሚዎች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖሩና በሥራቸው ወይም በሚኖሩባቸው ማኅበረሰቦች እንቅፋቶች ወይም መሰናክሎች አያጋጥሙአቸውም ብሎ እስከ መናገር ድረስ ይሄዳል፡፡ ሞዴሉ ራስን ችሎ መኖርን ሲያበታታ የግለሰቡን አቅም ለይቶ በማወቅና በማሳደግ የአካል ጉዳትን አጋጣሚ ለማሳነስ ይሻል፡፡ ይህ እክል ካለበት ግለሰብ ይልቅ ኅብረተሰብን መልሶ እንደ ማቋቋም ሊገለጽ ይችላል፡፡

    የገለጻ ማሳያ 10ን ተጠቀመው በአሁኑ ጊዜ አካል ጉዳት በላቀ ሁኔታ እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ እየታየ መሆኑን በማስመር የሰብአዊ መብቶችን ትርጕም ይግለጹ፡፡ ሰብአዊ ክብርን ማእከል ያደረገው የሰብአዊ መብቶች ሕግ መሠረታዊ ሃሳብ ሰዎች ሁሉ እኩል መብቶች፣ በተለይ በመሥራት መብት ሙሉ የተጠቃሚነት መብት፣ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማንኛውም ሰው ሰብአዊ ፍጡር ነው የሚለውን ቀላል ግን ደግሞ በወሳኝ ሁኔታ አስፈላጊ ጽንሰ ሃሳብ ያንጸባርቃል፡፡ ዜግነታቸው፣ የመኖሪያ ቦታቸው፣ ፆታቸው፣ ብሔራዊ ወይም ጐሣዊ ማንነታቸው፣ ቀለማቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ቋንቋቸው፣ አካል ጉዳታቸው ወይም ሌላ ሁኔታቸው ምንም ይሁን ሰብአዊ መብቶች ለሁሉም ሰብአዊ ፍጡራን የተገቡ ናቸው፡፡ ማንኛውም ሰው መድልዎ ሳይኖር ሰብአዊ መብቶችን የመጠቀም መብት አለው፡፡ ለእነዚህ የግለሰቦች መብቶች መልስ በመስጠት ረገድ መንግሥታት ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ፣ የማክበርና የመፈጸም ግዴታ አለባቸው፡፡ መንግሥታት በተወሰኑ መንገዶች እንዲሠሩ ወይም ሰብአዊ መብቶችን፣ የግለሰቦችን ወይም የቡድኖችን መሠረታዊ ነፃነቶች ለማሳደግና ለመጠበቅ አንዳንድ ነገሮችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ ግዴታዎችን ያስቀምጣል፡፡ ይህ የአካል ጉዳት ጉዳዮችን እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መልሶ የመመዘን ሁኔታ በዓለም አቀፍና በብሔራዊ ሕጎች ዋነኛ ለውጦችን እያበረታታ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአካል ጉዳተኞች መብቶች በአጠቃላይ፣ እንዲሁም በተለይ በተቀረጹ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች አማካይነት መጠበቅ ያለባቸው መሆኑ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ብሔራዊ መንግሥታት ይህን በሕግ አወጣጣቸው አማካይነት የሚቻል ማድረግ ይችላሉ፡፡

    የ1946ቱን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጠቅላላ መግለጫ፣ የ1966ቱን የተመድ ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳንና በዚሁ ዓመት የወጣውን የተመድ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ቃል ኪዳን የመሳሰሉ ከ1940ዎቹ አጋማሽ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ የጸደቁት የሰብአዊ መብቶች ቻርተሮችና ድንጋጌዎች አካል ጉዳትን ለይተው አይጠቅሱም፡፡ አካል ጉዳተኞችን የሚገጥሙአቸው አስቸጋሪ ነገሮች፣ ማኅበራዊ መገለላቸው፣ እንዲሁም የሚፈጸምባቸው መድልዎ የሰብአዊ መብቶች ጥያቄን እንደሚፈጥር የታሰበው ከ1970ዎቹ ወዲህ ነው፡፡ ከማኅበራዊ ደህንነት አቀራረብ በሰብአዊ መብቶች ላይ የተመሠረተ ወደ ሆነው የተደረገው ሽግግር ከ1980ዎቹ ወዲህ እንደ ተመድና የአውሮፓ ምክር ቤት በመሳሰሉ ድርጅቶች በጸደቁት ብዛት ባላቸው - አዘውትሮ አስገዳጅ ባልሆኑ - ሰነዶች እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ቻርተሮች፣ ድንጋጌዎችና ተነሣሽነቶች አካል ጉዳተኞችን በተለየ ሁኔታ በመጥቀስ ተንጸባርቆአል፡፡ እነዚህ ሰነዶች የ1992ቱን የአውሮፓ ምክር ቤት የአካል ጉዳተኞች ግልጽ ፖሊሲን እና የ1993ቱን ዕድሎችን ለአካል ጉዳተኞች እኩል በማድረግ ዙሪያ የተመድ መደበኛ ደንቦችን ያካትታሉ፡፡

    በማኅበራዊ ልማት፣ በሰብአዊ መብቶችና በመድልዎ አልባነት መስክ በታሪካዊው አቀራረብ ላይ ተመሥርቶ፣ እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና በማኅበራዊ ልማት ኮሚሽን የቀረቡትን መሪ ሃሳቦች ግምት ውስጥ በማስገባት የአካል ጉዳተኞችን መብቶችና ክብር ለማሳደግና ለማስጠበቅ አጠቃላይና ዓይነተኛ ለሆነ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ሃሳቦችን ለመመልከት ለሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል መንግሥታትና ታዛቢዎች ክፍት የሆነ ጊዜያዊ (አድ ሆክ) ኮሚቴ እንዲቋቋም ታኅሣሥ 19 ቀን 2001 (እ.አ.አ) የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ 56/168ን አሳለፈ፡፡ ጊዜያዊ ኮሚቴው በሰኔ 2003 ባደረገው ሁለተኛ ስብሰባው እንዲህ ዓይነቱን ድንጋጌ በማዳበሩ ሂደት ለመቀጠል ውሳኔ ተላልፎአል፡፡ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ድንጋጌና አብሮት የወጣው ተጨማሪ ፕሮቶኮል ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ታኅሣሥ 13 ቀን 2006 የጸደቀ ሲሆን መጋቢት 30 ቀን 2007 ለፊርማ ክፍት ሆኖአል፡፡ ድንጋጌው ከተጨማሪ ፕሮቶኮሉ ጋር ግንቦት 3 ቀን 2008 የጸና ሕግ ሆኖአል፡፡ ይህ የአካል ጉዳተኞችን በሰብአዊ መብቶችና በመሠረታዊ ነፃነቶች ሙሉ ተጠቃሚነት ለማሳደግ፣ ለመጠበቅና ለማረጋገጥ፣ አንዲሁም ለተፈጥሮአዊ ክብራቸው ከበሬታን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ዐቢይ ምዕራፍን አሳይቶአል፡፡

    ብዛት ያላቸው ነባር የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች የአካል ጉዳተኞችን መብቶች እዲያካትቱ ሆነው በመሻሻል ላይ በመሆናቸው፣ አጠቃላይና አካል ጉዳት ነክ የሆኑ አዳዲስ ሰነዶችም እየጸደቁም ስለ ሆነ፣ ከማኅበራዊ ደህንነት ወደ ሰብአዊ መብቶች ሕግ አቀራረብ የሚደረጉ ተመሳሳይ ሽግግሮች በአካባቢና በብሔራዊ ደረጃ እየተካሄዱ ናቸው፡፡

  •  
    አማራጭ መልመጃ፡- ተሳታፊዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁባቸውን ዐሠርት ዓመታት (ለምሳሌ 1940ዎቹ፣ 1950ዎቹ፣ 1960ዎቹ፣ ወዘተ) መሠረት በማድረግ በትናንሽ ቡድኖች ይከፋፍሉአቸው፡፡ እያንዳንዱ ቡድን አንድ ሪፖርት አቅራቢ ወይም መዝጋቢ መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ለእያንዳንዱ ቡድን የፍሊፕቻርት ወረቀትና መጻፊያ ማርከር መስጠት ያስፈልግዎታል፡፡ የገለጻ ማሳያ 11ን ተጠቅመው እያንዳንዱ ቡድን የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገጠመኞቹን እንዲያስታውስና የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንዲመልስ ያድርጉ፡- የጊዜው ወረቶች/ፋሽኖች ምን ነበሩ? ሳይንሳዊ ግኝቶቹ ምን ነበሩ? ዋነኛ ታዋቂዎቹ እነማን ነበሩ? እርስዎ አካል ጉዳተኞችን ያዩት የት ነው? መልሶች ሲመጡ መዝጋቢው ግለሰብ በተገላጭ ወረቀቱ ላይ መጻፍ ይኖርበታል፡፡ በመልመጃው ማብቂያ ሪፖርት አቅራቢው ግለሰብ የቡድኑን መልሶች ማጋራት ይኖርበታል፡፡ የተለመዱ ርእሶችን ለመለየት አሥር ደቂቃ ይወሰዱና በዐሠርት ዓመታቱ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የሕዝብ አስተሳሰቦችና ገጠመኞችን ይወቁ፡፡
  • ከ1940ዎቹ አጋማሽ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ የጸደቁት የሰብአዊ መብቶች ቻርተሮችና ድንጋጌዎች አካል ጉዳተኞችን በተለይ እንደማይጠቅሱ፣ አካል ጉዳተኞችን የሚያጋጥሙአቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ መታሰብ የጀመሩት ከ1970ዎቹ ወዲህ እንደ ሆነ ለተሳታፊዎች የያስረዱ፡፡
  • የገለጻ ማሳያ 12ን ተጠቅመው የአካል ጉዳት አጋጣሚን እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ከፍ ለማድረግ የተደረጉትን አዎንታዊ ለውጦች አጉልተው ያሳዩ፡፡
  • አካል ጉዳትን እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የሚያጠናክረውን በጣም የቅርብ ጊዜ የተመድ ድንጋጌን አጉልቶ ለማሳየት የገለጻ ማሳያ 13ን ተጠቅመው ይህን ክፍል ይደምድሙ፡፡