የሥልጠና ዝርዝር
2.4. መደበኛ ገለጻ በሕግ ውስጥ የአካል ጉዳት ስፍራ
- የአካል ጉዳት መድልዎ አልባ መርሆ በሕግ ውስጥ መጠቃለል በሚችልበት ዙሪያ የተለያዩ አማራጮች እንዳሉ ለተሳታፊዎች ያሳዩ፤ አማራጮቹ ሕገ መንግሥት (መንግሥታት ለዜጎቻቸው ኃላፊነት እንዳለባቸውና በመንግሥቱ የተረጋገጡትን መብቶች የሚያብራሩት በአንድ አገር ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጡት ጽንሰ ሃሳቦች)፣ ፍትሐ ብሔር ወይም ሲቪል ሕግ (ከግለሰቦች የግል መብቶች ጋር የተያያዙትና እነዚህን የሚያካትቱት ሕጋዊ እርምጃዎች)፣ የሠራተኛ ሕግ (የሥራ ስምሪት ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕጎችና ደንቦች)፣ የወንጀለኛ ሕግ (እንደ ስርቆት ያለ ወንጀልን የሚመለከቱ) ወይም የመቅጫ ሕግ (አንድን ድርጊት የሚከለክሉና ለመፈጸሙም ቅጣትን የሚጥሉ) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መዳሰስ ባለበት ጉዳይ ስፋት ላይ በመመርኮዝ መንግሥታት ይህን በአንድ አቀራረብ ውስጥ ለማጠቃለል ወይም ዘርፈ-ብዙ አቀራረብ ሊመርጡ ይችላሉ፡፡
በጣም ከፍተኛው የሕግ ደረጃ «ሕገ መንግሥት» እንደ ሆነ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ይህ የመድልዎ አልባ መርሆ አመዳደብ ጉዳዩ በኅብረተሰብ ውስጥ ስላለው ከፍተኛ ግምት ብዙ እንደሚናገር ለተሳታፊዎች አጽንኦት ይስጡ፡፡ የገለጻ ማሳያ 18ን በመጠቀም የሕጎች ዓይነቶችና ደንቦች ሊይዙ የሚችሉአቸአውን መልኮች ይዘርዝሩ፡-
የ1988ቱ የብራዚል ሕገ መንግሥት አካል ጉዳተኞች በግልጽ የተጠቀሱበትን አንድ ምሳሌ ይሰጣል፡፡ የዜጎችን መብቶችና የመንግሥቱን ግዴታ የሚመለከቱት የሕገ መንግሥቱ ምዕራፎች ሁሉ አካል ጉዳተኞችን በተለይ የሚጠቅሱ አንቀጾች አሉአቸው፡፡ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ያሉባቸው ግዴታዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ አካል ጉዳተኞችን እስከ ተመለከተ ድረስ የቅጥርን መስፈርቶች ወይም የክፍያ ልዩነቶችን አስመልክቶ የሚፈጸም መድልዎን ይከለክላል፡፡ ከዚህ ሌላ በ1988 የታተመው አዲሱ የፌዴራል ሕገ መንግሥት ግዛቶችና ከተሞች ስለ አካል ጉዳተኞች አንቀጾችን ለማካተት ሕጎቻቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው አመልክቶአል፡፡
አንድ ብሔራዊ ሕገ መንግሥት በጥቅሉ የአንድ አገር ከፍተኛው ሕግ እንደ ሆነና በሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣኞች ላይ አስገዳጅ መሆኑን እንዲገነዘቡ ተሳታፊዎችን መርዳት ይቀጥሉ፡፡ ስለዚህ ሕጎችና ፖሊሲዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተስማሙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አንዳንድ አገሮች አካል ጉዳትን በሕገ መንግሥታዊ ደንቦቻቸው እንዳካተቱ ለማሳየት የገለጻ ማሳያ 19ን ይጠቀሙ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ደንቦች በብሔራዊ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ሁኔታ አስመልክቶ ከፍተኛ ግምት ያለው መልእክት እንደሚልኩና ሌሎች ሕጎች እንዲሁም ፖሊሲዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጣጣሙ ለማረጋገጥ እንደሚሹ በማጠናከር ያስረዱ፡፡ ልዩ የአገር ምሳሌዎችን ከመጥቀስዎ በፊት የሕገ መንግሥታዊ መብቶች መጽናትና ውጤት በአንድ አገር የሕግ ባህልና ሥርዓት ውስጥ ጥቅም ላይ በዋሉት ቃላት አመራረጥ ላይ እንደሚመረኮዝ ለተሳታፊዎች ያስስቡ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ደንቦችን ለመለየት ሦስት መንገዶች እንዳሉ ለተሳታፊዎች ይግለጹ፡፡
የገለጻ ማሳያ 20ን በመጠቀም (እንዲሁም ከዐውደ ንባቡ ገጽ 9 ላይ ካሉት ተጨማሪ ምሳሌዎች በመጥቀስ) የአካል ጉዳተኞችን ማኅበራዊ ውህደት ለማሳደግ የመጀመሪያው መንገድ መንግሥቱ ለልዩ እርምጃዎች ፍላጎቶች መልስ እንዲሰጥ እና/ወይም እርምጃ እንዲወስድ እንደሚይጠይቅ ያስረዱ፡
የገለጻ ማሳያ 21ን (እንዲሁም ከዐውደ ንባቡ ገጽ 10 ተጨማሪ ምሳሌዎችን) በመጠቀም ሁለተኛው መንገድ በአካል ጉዳት ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸም መድልዎን መከልከል እንደ ሆነ ያስረዱ፡፡
የገለጻ ማሳያ 22ን (እንዲሁም ከዐውደ ንባቡ ገጽ 10 ተጨማሪ ምሳሌዎችን) በመጠቀም ሦስተኛው መንገድ ለሕገ መንግሥታዊ መብቶች ተፈጻሚነት እንደ እንባ ጠባቂ (ኦምቡድስማን) ተቅዋም እና/ወይም የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ የበላይ ተመልካች አካላትን ለመፍጠር እንደ ሆነ ያስረዱ፡፡
- የአካል ጉዳት መድልዎ አልባ ደንቦችን ለማጠቃለል ሁለተኛው መንገድ የፍትሐ ብሔርና የሠራተኛ ሕጎችን መጠቀም እንደ ሆነ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ሕጎች የመድልዎ አልባ ሕጎችን ወይም የሥራ ስምሪት መብቶች እንደሚሰጡት እንደ ኮታ ሕጎች ያሉ መልኮች መያዝ ይችላሉ፡፡ የገለጻ ማሳያ 23ን በመጠቀም ለሕጉ ስፋት የሚቻሉ አማራጮችን ያሳዩ፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ወይም የቅጣት ሕግን አቀራረብ ያጠቃልሉ፡፡ ይህ አቀራረብ መድልዎ በትክክል እንደ ተፈጸመ በተረጋገጠ ጉዳይ መቀጫዎችን ወይም እስራትን እንደሚያስከትል ያስረዱ፡፡ አሠሪዎች መድልዎ ለማድረግ እንዳሰቡ እስካላረጋገጡ ድረስ ይህ አቀራረብ ለአካል ጉዳተኛ ሠራተኞች በተለይ ውጤታማ እንዳልሆነ ያረጋግጡ፡፡ እንዲህ ያሉት ደንቦች ጠንካራ የሆኑ አሳማኝ መልእክቶችን መላክ እንደሚችሉ ይናገሩ፡፡
እያንዳንዱ ብሔራዊ ሥርዓት ማኅበራዊ ጉዳዮችን በወንጀልነት የሚያይበት የየራሱ አቀራረብ እንዳለው በማስረዳት የገለጻ ማሳያ 24ን ይጠቀሙና የፈረንሳይ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 224ን ያሳዩ፡፡ ከዚህ ሌላ በአካል ጉዳት ላይ ተመርኩዞ የሚፈጸም መድልዎን የሚከለክሉ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ደንቦች ያሉአቸውን አገሮች ያሳዩ፡፡ እነዚህም ፊንላንድን፣ ፈረንሳይን፣ ሉክሰምበርግና ስፔይንን ያካትታሉ፡፡ በተጨማሪም እዚህ አገሮች (ከሉክሰምበርግ በቀር) ጸረ መድልዎ ደንብ በሌሎች የሕጎቻቸው ክፍሎች ውስጥ አስገብተዋል፡፡
በመዝጊያው አንዳንድ መንግሥታት ከወንጀለኛ መቅጫ ይልቅ በፍትሐ ብሔርና በሠራተኛ ሕጎች ውስጥ አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ደንቦች አጽድቀዋል፣ ነገር ግን ወንጀል ነክና አስተዳደራዊ ቅጣቶችን በእነዚህ ሕጎች ውስጥ ያካትታሉ፡፡
ማሳሰቢያ፡- ተሳታፊዎች እንዲመለከቱአው ሊሆኑ የሚችሉ ጠቋሚዎች በዐውደ ንባቡ ገጽ 12-13 ተካትተዋል፡፡