የሥልጠና ዝርዝር

3.5 መደበኛ ገለጻ - ማስረጃ የማቅረብ ግዴታን ማዛወር

  • በአንዳንድ ሕጎች ስር አንድ ግለሰብ በመድልዎ ምክንያት በደል ተፈጽሞብኛል ባይ ሲሆን ወይም ስትሆን በደሉ ለመፈጸሙ ማስረጃ ማቅረብ እንዳለበት ወይም እንዳለባት የገለጻ ማሳያ 59ን ተጠቅመው ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች እጅግ የማያስቸግር ሲሆን በሌሎች ደግሞ ፈጽሞ የማይቻል ነው፡፡

    ለመለየት ቀላል ሊሆን የሚችል የማስረጃ ዝርዝር እንዲፈጥሩ ተሳታፊዎችን ይጠይቁ፡፡ ይህ የሥራ ምደባን፣ ማስታወቂያዎችና የምልመላ ቁሳቁሶችን ሊያካትት ይችላል፡፡

    ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን የሚችል የማስረጃ ዝርዝር እንዲፈጥሩ ተሳታፊዎችን ይጠይቁ፡፡ ይህ በተጨባጭ ማስረጃ ከመሆኑ ይልቅ ይበልጥ በጥርጣሬዎችና በአለመተማመን ላይ የተመሠረቱ ሁኔታዎችን ያካትታል፡፡

  • ማስረጃ የማቅረብ ግዴታን አመልካቹ ወይም በሠራተኛው ላይ መጫን ፍትሐዊ ውጤት ለማግኘት ከማያስችሉት ታላላቅ እንቅፋቶች እንደ አንዱ እየታየ መሆኑን በአጽንኦት ያስረዱ፡፡

  • ብዙ አገሮች ማስረጃ የማቅረብ ግዴታን መድልዎ እንደ ፈጸመ ወደ ተነገረበት ወገን ማዛወር መጀመራቸውን ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ባሁኑ ጊዜ በብዙ የሕግ አስተዳደሮች መድልዎ እንደ ደረሰበት አቤቱታ ለሚያቀርብ አንድ አካል ጉዳተኛ መድልዎ እንደ ተፈጸመ የሚገመትባቸውን ጭብጦች በፍርድ ቤት ወይም ብቃቱ ባለው ባለሥልጣን ፊት ማቅረብ ይበቃል፡፡ ከዚህ በኋላ መድልዎ እንዳልተፈጸመ የማረጋገጡ ተግባር መድልዎ ፈጽሞአል ተብሎ የተከሰሰው ግለሰብ ፋንታ ነው፡፡ ይህ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ተገላቢጦሽ መድልዎ አልባ ሕግን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ ተገላቢጦሹ አንዴ ክስ ከቀረበ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታውን መድልዎ አደረገ በተባለው ወገን ላይ ያስቀምጣል፡፡

    ለምሳሌ አንዲት ማየት የተሳናት የሕግ ባለሙያ አገሯን በዲፕሎማቲክ ጓድ ውስጥ ለማገልገል ፈተና ትወስድና ከሦስቱ ከፍተኛ ደረጃዎች በአንዱ ታልፋለች፡፡ ይሁንና በመሾም ፋንታ ትታለፍና ከእርሷ ያነሱ ደረጃዎችን ያመጡ ሰዎች ምደባዎችን ያገኛሉ፡፡ የግልባጭ ምሳሌ ከሥራ መደቡ በተባረረ የቀዶ ጥገና ሀኪም የተከሰሰ ሆስፒታል ይሆናል፡፡ የቀዶ ጥገና ሀኪሙ ላለበት አካል ጉዳት ሆስፒታሉ ማመቻቸት እንዳቃተው ክስ ያቀርባል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱ የመጠጥ ሱስ በመሆኑ በሌሎች ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በሚል ጭብጥ ላይ በመመርኮዝ ሆስፒታሉ ያባርረዋል፡፡

    በመዝጊያው የገለጻ ማሳያ 60ን ተጠቅመው ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ መድልዎን በሚያስከትሉ የሥራ ስምሪት መድልዎ ጉዳዮች ማስረጃ የማቅረብ ግዴታን ተገላቢጦሽ የሚያስችሉ ሕጎች ወይም ማሻሻያዎች አገሮች በሕጎቻቸው ውስጥ እንዲያስገቡ በመጠየቅ የአውሮፓ ኅብረት ያስቀመጠውን አርአያ ለውጥ ይግለጹ፡፡

    በ2003 አሥራ አምስቱ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ሁሉ ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ መድልዎን በሚያስከትሉ የሥራ ስምሪት መድልዎ ጉዳዮች ማስረጃ የማቅረብን ግዴታን ተገላቢጦሽ የሚያስችሉ ሕጎች ወይም ማሻሻያዎች በሕጎቻቸውና በሌሎች ሕግ ነክ ሰነዶቻቸው ውስጥ እንዲያስገቡ ተጠይቀው የነበረ ሲሆን እንዲሁም ወደ ኅብረቱ የሚገቡ አዳዲስ መንግሥታትም ይህን መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ በ2000 ዓ/ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀው የአውሮፓ ኅብረት ሕግ (መመሪያ) የተከተለ ሲሆን አካል ጉዳተኛውን የሥራ አመልካች ወይም ሠራተኛ በመደገፍ ከ2003 በኋላ የአካል ጉዳት መድልዎ ጉዳዮች ማስረጃ በማቅረብ ግዴታ ተገላቢጦሽ ላይ እንዲመረኮዙ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

    መድልዎ አልባ ሕጎች አካል ጉዳትን ጥበቃ እንደሚደረግለት ጭብጥ መጥቀስ እንደሚኖርባቸው፤ መድልዎን የሚከለክሉ ሕጎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ መድልዎን፣ እንግልትን፣ ትእዛዝና ማነሣሳትን ጨምሮ ሁሉንም የመድልዎ ዓይነቶች መሸፈን እንደሚኖርባቸው፤ ተመጣጣኝ ማመቻቸት ለዘመናዊ ጸረ መድልዎ ሕግ ቁልፍ ክፍል እንደ ሆነና መሰጠት እንደሚኖርበት፤ እንዲሁም ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ መድልዎ ፈጽመዋል ወደ ተባሉት ወገኖች መዛወር እንደሚኖርበት አጽንኦት በመስጠት ይህን ክፍለ ትምህርት ይደምድሙ፡፡