የሥልጠና ዝርዝር

6.1 መደበኛ ገለጻ - ከማኅበራዊ አጋሮችና ከሲቪል ኅብረተሰብ ጋር መመካከር

  • የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ለማሳደግ የታቀዱ ሕጎችን ለማርቀቅ ወይም ለማሻሻል እንዲሁም እነዚህን ሕጎች ለመተግበር ፖሊሲዎችን ለማውጣት በሚሹበት ጊዜ የሕግና ፖሊሲ አውጪዎች በስፋት መመካከር እንደሚኖርባቸው ለተሳታፊዎች አጽንኦት በማድረግ ይህን ክፍል ይጀምሩ፡፡ በስፋት የተደረገ ምክክር የሕግና ፖሊሲ አውጪዎችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ካለው አውቀት ለመጠቀም እንደሚያስችላቸውና የጸደቀውን ማንኛውንም ሕግና ፖሊሲ ውጤታማነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳቸው አጽንኦት ለመስጠት የገለጻ ማሳያ 99ን ይጠቀሙ፡፡
  • ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር መመካከር
    እንደ እውነቱ ሕግ በማርቀቅ ሂደት ከአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች መረጃ ለመሰብሰብና እነርሱንም ለማሳተፍ የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ ለተሳታፊዎች ሲያስረዱ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ የዐውደ ንባቡን ክፍል 6.1.1 በመጥቀስ በመጀመሪያ አካል ጉዳተኛ ግለሰቦችን ከሚወለክሉ ማኅበራት ጋር፣ ከዚያም በሁለተኛ ደረጃ ከራሳቸው ከአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ወይም የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች ከሚወክሉ የፓርላማ ተወካዮች ጋር በመመካከር መረጃ መሰብሰብና ተሳትፎአቸውን መጠየቅ እንደሚቻል ለማሳየት የገለጻ ማሳያ 100ን ይጠቀሙ፡፡

    ከአካል ጉዳኞች ማኅበራት ጋር ለመመካከር ሌሎች አቀራረቦች፡፡
    «
    በቅርብ ዓመታት አንዳንድ አገሮች ሕግ፣ ወዘተ. ማርቀቅን በሚመለከት የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን ከማማከር አልፈው የመንግሥቱ ክፍል በመሆን የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች በሚወክሉ ጉዳዮች በቀጥታ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ፖለቲካዊ ድምጽ ለማረጋገጥ ሁነኛ ጥረት ያደረገች የመጀመሪያዋ አገር ደቡብ አፍሪካ ነበረች፡፡ በ1999 አገሪቱ አካል ጉዳተኛ የሆኑ 10 የፓርላማ አባላት የነበሩአት ሲሆን ይህም በዓለም ከማንኛውም አገር እጅግ ከፍተኛው ቁጥር ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ ወይም ድንገተኛ ክስተት አይደለም፤ ይልቁን ምንም የአናሳዎች ውክልና ያልነበረባቸውን ያለፉትን የአፓርታይድ ልምዶች ለማውደም የብዙኀኑ ፓርቲ የሆነው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ ካደረጋቸው ጥረቶች አንዱ ክፍል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በፓርላማ ውስጥ በተያዙት የአካል ጉዳት መቀመጫዎች ምክንያት ውክልናው የተረጋገጠ ነው፡፡ ብሔራዊ ኮንግሬሱ በተለያዩ መልክአ ምድራዊ አካባቢዎች ያሉ በደንብ የሠለጠኑ አካል ጉዳተኞች ዝርዝር ለማርቀቅና ከዚያም ስማቸው በፓርቲው ብሔራዊ መዝገብ ለማስፈር አካል ጉዳተኞች ማኀበራትን ቀርቦ ጠይቆአቸዋል፡፡ ማስረጃዎቻቸውን ካረጋገጠ በኋላ ኮንግሬሱ ስሞቻቸውን በምርጫ ወረቀቶች ላይ አኑሮአል፡፡ ከምርጫው በኋላ ለመቀመጫዎቹ የተመረጡት ሰዎች እነርሱን ሊነኩአቸው በሚችሉት መስኮች ሁሉ የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎቶችና ስጋቶች መወከል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዛሬ አናሳ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አሠራሮችን ተከትለዋል፡፡ በኡጋንዳ ያለው ሂደት ከደቡብ አፍሪካው የተለየ ነው፡፡ ከ1996 ወዲህ ኡጋንዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሌሉበት ግን ደግሞ ሁሉም ወገኖች የራሳቸውን ተወካዮች የሚመርጡበት ሁሉን አቀፍ የሆነ የመንግሥት አሠራር እንቅስቃሴ ተቀብላለች፡፡ ይህን የጀመሩት አገሪቱን በአራት ክልሎች በመክፈል ሲሆን ከዚያም ውክልናው እንዴት መከናወን እንዳለበት በትክክል ወሰኑ፤ ይኸውም ለምሳሌ አንድ መቀመጫ በአካል ጉዳተኛ ሴት እንዲያዝ ሲወስኑ ለዚህም አንድ አካል ጉዳተኛ ሴት መወዳደር ትችላለች፡፡ ሚዛናዊ ውክልናን ለማረጋጥ የተቀሩት አራት መቀመጫዎች በወንዶችና በሴቶች ውድድር የሚደረግባቸው ሲሆን ከዚያም እያንዳንዱ ወረዳ ተወካዮቹን የሚልክባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ነበር፡፡ የፓርላማ አባላቱን የመምረጫው ጊዜ በደረሰ ጊዜ እያንዳንዱ ወረዳ አራት ሰዎችን - ማለት አንድ የማየት እክል ያለበት፣ አንድ መስማት የተሳነው፣ አንድ አካላዊ ጉዳት ያለበት፣ በመጨረሻም ሌላ ዓይነት አካል ጉዳት ያለበት- አንዲልክ ተጠየቀ፡፡ ሁሉም ወደ ምርጫ ጣቢያው ሄደው መግለጫቸውን የሚያረቅቁ ሲሆን በፓርላማ አባልነት ለማገልገል የሚሻ ሰው በዘመቻው ይቀጥልበታል፡፡ አካል ጉዳተኞች ብቻ ለተወካዮቻቸው ድምጽ መስጠት የሚችሉ ሲሆን የመረጡት ማንኛውም ሰው የመንግሥት ማጽደቂያ ሳያስፈልገው የፓርላማ አባል ይሆናል፡፡ የራሳቸውን የፓርላማ አባላት በመምረጣቸው ብቻ ሳይሆን ካስፈለገ ወደ እነርሱ የሚሄዱባቸውን ከማኅበረሰባቸው ለተገኙ ሌሎች የፓርላማ አባላትም ድምጽ በመስጠታቸው ደግሞ ኡጋንዳውያን አካል ጉዳተኞች ትልቅ ተጽእኖ የማሳደር አቅም አላቸው፡፡»

    በመጀመሪያው ምሳሌ ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራትና ለእነርሱ ከቆሙ ድርጅቶች ጋር መመካር አስፈላጊ እንደ ሆነ ያስረዱ፡፡ የገለጻ ማሳያ 101ን ተጠቅመው ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጨምሮ መደረግ የሚኖርባቸውን ልዩ ትኩረቶች ይግለጹ፡፡

    • አካል ጉዳት ሳይኖርባቸው ሆነው የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎቶች ለመወከል ለሚሹት ከመሆኑ ይልቅ ማኅበራት የአካል ጉዳት ማኅበረሰቡ ወካይ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
    • ማኅበራት የሴቶችን፣ የሌሎች ጐስቋሎችና ውክልና የሌላቸውን የአካል ጉዳተኞች ወገኖች ስጋቶች እንዲያጤኑ መበረታታት ይኖርባቸዋል፡፡
    • አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን መወከል በማይችሉበት ጊዜ ምንም እንኳ በእነዚህ ሁኔታዎች አንዳንድ ሃሳቦችን ሊገልጹ የሚችሉትን አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ለማዳመጥ ማንኛውም ሙከራ መደረግ ቢኖርበትም ውክልናው በቤተሰብ አባላት ወይም በተሟጋቾች አማካይነት መሆን ይችላል፡፡

    አካል ጉዳተኛው ማኅበረሰብ በጣም ቅይጥ መሆኑን ተሳታፊዎች መገንዘባቸውን ያረጋግጡ፡፡ የተለያዩ አካል ጉዳቶች ያሉባቸውን ሰዎች የሚወክሉ በርካታ የተለያዩ ድርጅቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከሁሉም ወካይ ድርጅቶች ምክር መጠየቅ የሚኖርበት ሲሆን ምክክሩ በብሔራዊ የአካል ጉዳት ምክር ቤት ወይም በብሔራዊ የአካል ጉዳት ማኅበራት ኔትወርክ ደግሞ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡

    የተለዩ ችግሮች፣ ጉዳዮች፣ መቀረፍና መልስ ማግኘት ያለባቸውን ፍላጎቶች እንዲሁም የለውጥ አማራጮችን የሚያወያይ እንደ መነሻ ምክክሩ መጀመር የሚችልበት አንዳንዴ ነጭ ወረቀት እየተባለ የሚጠራው የአቋም መግለጫ ወረቀት መዘጋጀት እውን መሆን ለሚችል ስትራቴጂ ጠቃሚ እንደሚሆን ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ሰፋ ያሉ የአካል ጉዳት ድርጅቶች በዚህ የአቋም መግለጫ ወረቀት ላይ አስተያየት እንዲሰጡና እንዲወያዩ በተለይ ሊጋበዙ ሲችሉ ባለሥልጣኖች የማያውቁአቸው አነስተኛ ድርጅቶች የሚፈልጉ ከሆነ መልስ የመስጠት ዕድሉ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ይህ ዝግጅት እንዲሠራ የአቋም ወረቀቱ በስፋት መሰራጨትና ምክክሩን በሚመለከት በቂ ማስተዋወቂያ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ለሕዝብ የሚቀርቡ የአስተያየት ጥያቄዎች በዚህ ቀዳሚ ደረጃ ላይ ክርክሩን
    ያበለጽጉታል፡፡

     
    አማራጭ መልመጃ፡-በአገራቸው የአካል ጉዳትና ሥራ ስምሪት መድልዎ አልባ ሕግ መውጣትን በመደገፍ የአቋም መግለጫ ወረቀት (ነጭ ወረቀት) በማውጣት ረገድ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ለተሳታፊዎች በመግለጽ ይህን መልመጃ ይጀምሩ፡፡ ተሳታፊዎቹን 5 ግለሰቦች በሚይዙ አነስተኛ ቡድኖች ይከፋፍሉአቸው፣ እያዳንዱን ቡድን የማውጫ ይዘትን ተጠቅሞ ጽሁፍ እንዲያረቅቅ ይጠይቁ፡፡ የጽሁፉ ዓላማ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት በሚመለከት መድልዎ አልባ ሕግ ዕቅድ ለማውጣት አንደ ሆነ ያስረዱ፡፡ ፈታኝ የሚሆንባቸው በአንድ አጠቃላይ ዕቅድ ውስጥ ምን መጠቃለል እንዳለበት ማሰቡ ላይ ነው፡፡ ጽሁፉን ለማዘጋጀት ለእያንዳንዱ ቡድን 45 ደቂቃ እንዲሁም በመልመጃው ላይ መግለጫ ለመስጠትና የጽሁፉን ዝርዝር ለመላው ክፍል ለማጋራት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ በመስጠት ሌላ 45 ደቂቃ ይስጡ፡፡

    ከአብዛኛው የአካል ጉዳት ማኅበረሰብ የሚገኘው ድጋፍ ለማንኛውም ተግባራዊ የፖሊሲ ስኬት ወሳኝ እንደ ሆነ ያስረዱ፡፡ ይህ ድጋፍ የማይኖር ከሆነ ለምሳሌ እንደ አካል ጉዳተኛ ባለመመዝገብ፣ ለገንዘብ ወይም ለቁሳቁስ ድጋፍ ባለማመልከት፣ ወይም የግል መብቶችን በፍርድ ቤት አማካይነት ለማስከበር ባለመፈለግ አካል ጉዳተኞች በፖሊሲው ላይ ያድሙ ይሆናል፡፡ ያለዚህ ድጋፍ ሕጉ ወይም ፖሊሲው የመክሸፍ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡

    የገለጻ ማሳያዎች 102-104ን በመጠቀም አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች በመመካከር ሂደቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ የፖሊሲ አውጪዎች ማድረግ የሚያስፈልጉአቸውን አንዳንድ ተጨማሪ ትኩረቶች አጉልተው ያሳዩ፡፡

    • አካል ጉዳተኞችና ማኅበሮቻቸው አንድም በሕግና በፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ ምክር ተጠይቀው ስለማያውቁ ወይም የተጻፈ መረጃን ለማንበበብና ለመረዳት በአካላዊ ሁኔታ ምክንያት ስለማይችሉ በረቂቅ ሕግና ፖሊሲ ተነሣሽነቶች ዙሪያ መልስና አስተያየት በቀላሉ ለመስጠት አይችሉ ይሆናል፡፡
    • የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን ተሳትፎ ለማሳድግ ልዩ ጥረቶች መደረግ
      ይኖርባቸዋል፡፡
    • በምክክሩ ዙሪያ የሚዘጋጅ ማንኛውም የተጻፈ ወይም የቃል መረጃ የታሰበውን ችግርና ያንን ችግር ለመፍታት የታቀዱ መሣሪያዎችን በግልጽ የሚያስቀምጥ በቂ መጠን ያለው የኋላ ዳራ መረጃ መያዝ ይኖርበታል፡፡
    • በተለይ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አስተያየቶቻቸውን መጠየቅ ባልለመዱበት ሁኔታ የአካል ጉዳተኞች አስተያየቶች ዋጋና ተቀባይነት ያላቸው የሆኑበት ጭብጥ ደግሞ አጽንኦት ሊደረግበት ይገባል፡፡
    • የተጻፈ መረጃ ከቀረበ አንዳንድ የአካል ጉዳት ዓይነቶች ላሉባቸው ሰዎች እንዲዳረስ እንደ ብሬል፣ የድምጽ ቴፖች፣ በጉልህ እትም የተዘጋጁ ጽሁፎች፣ ለማንበብ የቀለሉ ጽሁፎችና አጫጭር ማጠቃለያዎች የመሳሰሉ አማራጭ ይዘቶች ደግሞ ያስፈልጉ ይሆናል፡፡
    • እንዲህ ያሉትን አማራጭ ይዘቶች ለማቅረብ ከገንዘብ አኳያ ቀላል በማይሆንበት ጊዜ፣ ወይም  አግባብነት ያላቸው ካልሆኑ (ጽሁፉን በሚመረመረው ቡድን ካልተፈለገ) ዓይነ ስውራን የሆኑ ሰዎችንና የአእምሮ ጉዳተኞችን በመረጃውና በምክክሩ ሂደት የማሳተፍን አስፈላጊነት ሪፖርቱ ለአንባቢዎች ማሳሰብ ይኖርበታል፡፡
    • የሕግና የፖሊሲ ጉዳዮችን ከአካል ጉዳተኞችና ከማኅበሮቻው ጋር ለመወያየት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ወደተለያዩ  የአገሪቱ ክፍሎች ሊላኩ ይችላሉ፡፡ የተጻፉ የምክክር ሰነዶችን ለመቀበል ወይም ለማንበብ ለማይችሉ ሰዎች በመድረስ እንዲህ ያሉት ስብሰባዎች አስቀድሞ የተሰጠውን መረጃ ማጠናከርና ግልጽ ማድረግ
      ይችላሉ፡፡
      • በአማራጭ እንዲህ ያሉትን ስብሰባዎች እንዲመሩና የሰሙአቸውን አስተያየቶች እንዲዘግቡ የመንግሥት ባለሥልጣኖች አካል ጉዳተኞችን ማሠልጠን ይችላሉ፡፡ ይህ ከአካል ጉዳት ማኅበረሰቡ ጋር ግልጽና መደበኛ ያልሆነ ውይይትን ያስከትላል፡፡
      • እንዲህ ባሉት ስብሰባዎች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ተሳትፎ ለማመቻቸት የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ሊፈለግ ይችላል፡፡ በቂ ማሳሰቢያና ድጋፍ ከተሰጣቸው የአካበቢ ማኅበረሰቦች እነዚህን አስተርጓሚዎች ማቅረብ ይችሉ ይሆናል፡፡
    • ስብሰባዎችን ማካሄድ ካልተቻለ በሕግና በፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ ክርክር ለማነሣሳትና አስተያየት ለማግኘት የሬድዮ ጭውውት ፕሮግራሞች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

    በአካል ጉዳት ጉዳዮች ዙሪያ መንግሥትን ለማማከር አየርላንድ የወሰደችውን የነፃ ኮሚቴ አቀራረብ የሚያሳየውን በዐውደ ንባቡ ገጽ 59 የቀረበውን ምሳሌ በመጥቀስ ይህን ንኡስ ክፍል ይደምድሙ፡፡ ነፃ ኮሚቴዎች የአካል ጉዳተኞችን ድምጽ በሕዝባዊ የፖሊሲ አወጣጥ ውይይቶች የታዋቂነት ቦታ እንዳለው በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ አሠራር እንደ ሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም አሠራሩ ለፖሊሲ ማውጣት ሂደቱ ወሳኝ ሊሆኑ ከሚችሉ አንዳንድ ዒላማ ከሆኑ ወገኖች መረጃ ለመሰብሰብ፣ ለመተንተንና ለማቀነባበር ገለልተኛና የማያዳላ መሣሪያ ይሰጣል፡፡

    «በአየርላንድ በአካል ጉዳት ፖሊሲ ላይ መንግሥትን ለማማከር ነፃ የሆነ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ የኮሚቴው አባላት ሁሉ አካል ጉዳት ያለባቸው ወይም ራሳቸውን ለመወከል የማይችሉ አካል ጉዳተኞች ወላጆች ነበሩ፡፡ ኮሚቴው በመላው አየርላንድ በመዘዋወር ስለ ወደፊቱ የአካል ጉዳት ፖሊሲ ለመወያየት ሕዝባዊ መድረኮችን አዘጋጅቶአል፡፡ ኮሚቴው በአየርላንድ የአካል ጉዳት ፖሊሲ እንዴት መዘጋጀት እንደሚኖርበት በራሱና ከሕዝብ ባገኛቸው አስተያየቶች ላይ የተመሠረተ ረጅም ሪፖርት በማቅረብ ሥራውን ደምድሞአል፡፡»

  • ከአሠሪዎችና ከአሠሪዎች ማኅበራት ጋር መመካከር፡፡
    የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ለማሳደግ አንድ ሕግ ወይም ፖሊሲ የሚያስከትላቸው ብዙ ግዴታዎች በአሠሪዎች ላይ እንደሚወድቁ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ በአሠሪዎች ላይ ከሚያመጣው ፍጹም ተጽእኖ በመነሣት ሕጉን ወይም ፖሊሲውን ከማጽደቅ ወይም ከማሻሻል አስቀድሞ የአሠሪዎችን አስተያየት መገንዘብና፣ በሚቻልበት ጊዜ፣ ከአሠሪዎች ጋር በመተባበር መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ እይታ በሕግና ፖሊሲ ማውጣቱ ሂደት የአሠሪዎችን ተወካዮች ማሳተፍ ለምን አስፈላጊ እንደ ሆነ ተሳተፊዎችን ይጠይቁ - አንድ የአሠሪ ተወካይ በማርቀቁ ሂደት ለምን ግብአት እንዲኖረው ይፈልጋል? ተሳታፊዎችን መልሶች በተገላጭ ወረቀቱ ላይ መመዝገብዎን ያረጋግጡ፡፡

    የዐውደ ንባቡን ክፍል 6.1.2 በመጥቀስ የአሠሪ ማኅበራትን ከማሳተፍ ጋር የሚገናኙ አንዳንድ መሠረታዊ መረጃዎችን ለማሳየት የገለጻ ማሳያ 105ን ይጠቀሙ፡፡ ብዙ አገሮች ብዛት ያላቸውን አሠሪዎች የሚወክሉ ማእከላዊ የአሠሪዎች ማኅበራት እንዳሉአቸው ያስረዱ፡፡ ይሁንና ከአሠሪዎች ጋር የሚደረገው ምክክር በአንድ አካል የተወሰነ ይሆን ዘንድ አያስፈልግም፡፡ ምክክሩ እንደ ገጠርና ኢንዱትሪያዊ አሠሪዎች፣ የተለያዩ ዘርፎች አሠሪዎች፣ እንዲሁም ትላልቅና አነስተኛ አሠሪዎች ካሉ የተለያዩ የአሠሪዎች ዓይነቶችን ከሚወክሉ አካላት ጋር መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር በሚካሄደው ምክክር እንደሚደረገው ሁሉ አስተያየቶችን የሚጋብዘው የሕዝብ አቋም መግለጫ ወረቀት በስፋት መሰራጨት መልስን የማግኛ አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡

    የገለጻ ማሳያ 106ን የተዘረዘሩትን ለሚቻል አሠሪ ተሳትፎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎች መልሰው ይመልከቱ፡፡

    የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪትና እንዲሁም በሌሎች መስኮች ያሉትን በሚመለከት የሚወጡ አስገዳጅ ግዴታዎችን አሠሪዎች አዘውትረው እንደሚቃወሙ ሕግና ፖሊሲ አውጪዎች መገንዘብ እንደሚኖርባቸው ያስረዱ፡፡ ይልቁን የበጎ ፈቃድ መልካም አሠራር ደንብን አጠቃቀም ወደ መምረጥ ያዘነብላሉ፡፡ በመመሪያዎቹ እንደ ተገለጸው የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገሮች የበጎ ፈቃድ አቀራረብን አዘውትረው ከሞከሩ በኋላ ይህን የመሰለውን የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ማሳደጊያ አቀራረብ በመተው በምትኩ አስገዳጅ ግዴታዎችን በአሠሪዎች ላይ ጥለዋል፡፡

    ከገንዘብና ከማኅበራዊ እይታ አኳያ አካል ጉዳተኞችን መቅጠር መልካም የሥራ ልማድ በመሆኑ ዙሪያ አጽንኦት ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ በመግለጽ ይደምድሙ፡፡ ከዚያም የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች እንዴት በሌሎች ቦታዎች እንደ ሠሩና ከእነዚህ ፖሊሲዎች በአንዳንዶቹ ስኬት ዙሪያ ግልጽ መረጃ በመስጠት ይህ የሥራ ጉዳይ በስፋት በሚዳረስ የሕዝብ መረጃ ዘመቻ መሰራጨት እንደሚኖርበት በመግለጽ ይህን ክፍል ይደምድሙ፡፡

  • ከሠራተኞችና ከኅብረት ማኅበራት ጋር መመካከር
    ከአሠሪዎች ማኅበራት ጋር እንደሚደረገው ሁሉ ከማእከላዊው የኅብረት ማኅበር ድርጅትና ከዘርፍ የሠራተኛ ማኅበራት ጋር ምከክሮች መደረግ እንደሚኖርባቸው በማስረዳት በኅብረት ማኅበራት ዙሪያ የሚደረገውን ውይይት ይጀምሩ፡፡

    የገለጻ ማሳያ 107ን በመጠቀምና የዐውደ ንበቡን ክፍል 6.1.3 በመጠቀስ የሠራተኛ ማኅበራትን በሕግ ማርቀቅ ሂደቱ ለማስገባትና ለማሳተፍ መሠረታዊ ትኩረቶችን መልሰው ይመልከቱ፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት በአጠቃላይ የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን የሥራ ስምሪት ይደግፉ እንደ ሆነ የሕግና ፖሊሲ አውጪዎች ልብ ማለት እንደሚኖርባቸው ያስረዱ፡፡ አንዳንድ የሠራተኛ ማኅበራት የአባልነት አሠራራቸው አካል ጉዳት የሌለባቸውን ሠራተኞች ብቻ የሚያካትት ነው ብለው ስለሚያስቡ የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞች የሥራ ስምሪት ለማሳደግ በሚደረጉት የላቁ ጥረቶች አስጊ ሁኔታ የተደቀነባቸው መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የሠራተኛ ማኅበራት የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት በማሳደግ ረገድ አስቀድመው በንቃት አየተሳተፉና በውጤታማ ፖሊሲዎችና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ዋጋ ያለው የማስተዋል ችሎታቸውን እየሰጡ ይሆናል፡፡ በተለይ የተጠናከረ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞችን ወይም የአካል ጉዳቶች የመከሰት ዕድል ከፍተኛ በሆነበት አደገኛ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞችን የሚወክሉ አንዳንድ የሠራተኛ ማኅበራት ከተሀድሶና ከአካል ጉዳተኛ ሠራተኞች ወደ ሥራዎቻቸው መመለስ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን የመያዝ የመጀመሪያ ደረጃ ልምድና እውቀቱ አላቸው፡፡ በተጨማሪም ብዙ የሠራተኛ ማኅበራት በአንድ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ሠራተኞችን ስለሚውክሉ ወደ አካል ጉዳት ወይም ጉዳቶች ስለሚያመሩ የሥራ ሁኔታዎች እጅግ አዋቂ ናቸው፣ ስለዚህም እነዚህን ችግሮች በመከላከያ መንገዶች ዙሪያ አሠሪዎችና ሠራተኞችን ለመምከር በተሻለ አቋም ላይ ናቸው፡፡

    ዓለም አቀፍ የማሽን ባለሙያዎችና የጠፈር መንኰራኩር ሠራተኞች ማኅበር ምሳሌ
    «ዓለም አቀፍ የማሽን ባለሙያዎችና የጠፈር መንኰራኩር ሠራተኞች ማኅበር በእንግሊዝኛው ምኅፃረ ቃል IAM CARES—አያም ኬርስ ተብሎ የሚጠራውን የተሀድሶና የሥራ ስምሪት አገልግሎቶችን ለማስተዳደር ዓለም አቀፍ የማሽን ባለሙያዎች ማእከል ይረዳል በገንዘብም ይደግፋል፡፡ አያም ኬርስ በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ መደቦቻቸው ለተፈናቀሉ የአየር መንገድ ሠራተኞች ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል፡፡ ከአገልግሎቶቻቸው መካከል ከ25 በላይ የሚሆኑት ፕሮግራሞች በተለይ አካል ጉዳት ያጋጠማቸውን ሠራተኞች ወደ ሥራ መደቦቻቸው እንዲመለሱ ወይም በኢንዱስትሪው ውስጥ ወደ ሌሎች የሥራ መደቦች እንዲዛወሩ በመርዳት የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡ ኅብረቱ ነፃ የሥራ ስምሪት እርዳታና ሁሉም የአካል ጉዳት ዓይነቶች እና/ወይም ስር ሰደድ ሁኔታዎች ላሉባቸው ሰዎች የድጋፍ አገልግሎቶችን ከሚሰጥ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በሚገናኝ አያም ኬርስ ሶሳየቲ በሚባል አትራፊ ባልሆነ ድርጅት ይካሄዳል፡፡ በ1989 የዩናይትድ ስቴትስ አገልግሎቶች ባላቸው አትራፊ ያለመሆን ልምድና እውቀት የካናዳውያን አያም ኬርስ ማኅበር እንዲወለድ የረዱ ሲሆን በካናዳ ግን ዓለም አቀፍ የማሽን ባለሙያዎችና የጠፈር መንኰራኩር ሠራተኞች ማኅበሩ ከብረት ሠራተኞች ማኅበሩ ጋር አጋርነት የፈጠረ ሲሆን በካናዳ አገልግሎት አማካይነት የገንዘብ እርዳታ ይደረግለታል፡፡ አያም ኬርስ ማኀበር ወደ ሥራ ቦታ ሙሉ መካተት የሚመሩ ሙሉ የአገልግሎት ፈርጆችን የሚሰጡ አንዱ በብሪቲሽ ኮለምብያ ሌላው በሞንትርያል ኬቤከ የሚገኙ ሁለት ጽህፈት ቤቶች አሉት፡፡ አያም ኬርስ በካናዳ በሠራተኛ ማኅበር የሚረዳ ብቸኛው የሥራ ስምሪት ምደባ ፕሮግራም ነው፡፡»

    የሠራተኛ ማኅበራት አካል ጉዳት የሚያጋጥማቸው ሠራተኞች ባለ መብት የሆኑባቸውን የማኅበራዊ ዋስትና ጥቅሞች እንዲያገኙ መርዳት ቀዳሚ ሚናቸው እንደ ሆነ አዘውትሮ የሚሰማቸው መሆኑ ሌላው ጭብጥ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሠራተኛው በሥራ መደቡ እንዲቆይ ወይም ሌላ ሥራ እንዲያገኝ ከመርዳት ይልቅ ለጥቅሞች በመከራከር ረገድ ይበልጥ ችሎታው ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በማንኛውም ሁኔታ የሠራተኛ ማኅበራት ወደ ሥራ መመለስን በማሳደግ ረገድ የማበረታታት አቀራረቦችን ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡

    በዐውደ ንባቡ ገጽ 60 የሚገኘውን በአውሮፓ ኅብረት ጥቅም ላይ የዋለውን ሂደት የሚከተለውን ምሳሌ በማሳየት ይደምድሙ

    «የአውሮፓ ኅብረት አዲስ አውሮፓዊ የሥራ ሕግ እንዲወጣ ሃሳብ ለማቅረብ በሚያስብበት በማንኛውም ጊዜ በታቀደው መስክ ሕግ የማጽደቁን አስፈላጊነት እንደ አሠሪዎችና ሠራተኞች ተወካዮች ከመሰሉ ማኅበራዊ አጋሮች ጋር የመመካከር ግዴታ አለበት፡፡ የአውሮፓው ኅብረት ወደ ፊት ገፍቶ ለመሄድና በዚህ መስክ ሕግ ለማውጣት ከወሰነ በዚያ ሕግ ይዘት ላይ ማኅበራዊ አጋሮችን ማማከር አለበት፡፡»

  • አገልግሎት ሰጪዎችን ማማከር
    ተሳታፊዎች ከአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ጋር በመደበኛ ሁኔታ የሚሠሩ የአገልግሎት ሰጪዎችን ዓይነቶች ዝርዝር እንዲፈጥሩ ይጠይቁአቸው፤ መልሶቻቸውንም በተገላጭ ወረቀቱ ላይ ይመዝግቡ፡፡  መልሶች ነፃና የማኅበረሰብ አኗኗር ሰጪዎችን፣ የሥራ ስምሪት አገልግሎቶችና የሙያዊ ሥልጠና ሰጪዎችን፣ ማኅበራዊና የመዝናኛ አገልግሎት ሰጪዎችን፣ ወዘተ. ጨምሮ ሙሉ የሆነ አጠቃላይ እይታን መሸፈን ይኖርበታል፡፡ ምክክሩ እነዚህን ሁሉ አገልግሎት ሰጪዎች መሸፈን ይኖርበታል፡፡

     
    አማራጭ መልመጃ፡- ተሳታፊዎችን 4 እና 5 ግለሰቦችን በሚይዙ አነስተኛ ቡድኖች ይከፋፍሉአቸው፡፡ እያንዳንዱን ቡድን በመክፈቻ መልመጃው/ጥያቄው ተለይቶ በታወቀው አሠሪ/ድርጅት ተወካይ ዓይነት ይመድቡ፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የአካል ጉዳት የሥራ ስምሪት መድልዎ አልባ ሕግ እያረቀቀች ሲሆን እነርሱ የሚወክሉአቸውን ወገኖች በምክክሩ ሂደት እንዳይካተቱ ውሳኔ መተላለፉን ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ለምን በማርቀቁ ሂደት ምክር ሊጠየቁ እንደሚገባቸው ለመናገርና መከራከሪያቸውን ለመላው ክፍል ለማቅረብ እንዲዘጋጁ ለእያንዳንዱ ቡድን 30 ደቂቃ ይስጡ፡፡ ለእያንዳንዱ መከራከሪያዎችና ገለጻ 30 ደቂቃ ይፍቀዱ፡፡
     
    አማራጭ መልመጃ፡- ተሳታፊዎችን 4 እና 5 ግለሰቦችን በሚይዙ አነስተኛ ቡድኖች ይከፋፍሉአቸው፡፡ በመክፈቻው መልመጃ/ጥያቄ ተለይተው የታወቁትን አገልግሎት ሰጪዎች ዝርዝር በመጠቀም የአካል ጉዳት መድልዎ አልባ ሕግ ማውጣት ቢያስፈለግ በአገራቸው ውስጥ ምክር ሊጠየቁ የሚገባቸውን ትክክለኛ ድርጅቶች ዝርዝር እንዲያወጡ እያንዳንዱን ቡድን ይጠይቁ፡፡ የአካል ጉዳት ሕግ በማርቀቁ ሂደት በትክክል የሚሳተፉ ከሆነ የሚያወጡት ዝርዝር ጠቃሚ ምንጭ እንደሚሆን አጽንኦት በመስጠት ዝርዝሮቻቸውን እንዲሰበስቡ ለእያንዳንዱ ቡድን 45 ደቂቃ ይስጡ፡፡ ለተሳታፊዎች የመረጃ ክፍተቶች በሚኖሩበት ቦታ በዚያ መስክ ጠቃሚ ምንጭ የሆኑ ሰዎችን/ድርጅቶችን በመለየት ረገድ ሊረዱአቸው ስለሚችሉ ሰዎች/ድርጅቶች በጥልቀት እንዲያሰላስሉ ይንገሩአቸው፡፡ የመረጃ ክፍተቶች ምን ቦታ ላይ እንደ ነበሩና እርስ በርሳቸው ትስስር ፈጥረው እነዚህን ክፍተቶች በመሙላት ረገድ እንዲረዳዱ ተሳታፊዎችን በመጠየቅ የመጨረሻውን 15 ደቂቃ መልመጃውን ለማወያየት ይጠቀሙበት፡፡

    የዐውደ ንባቡን ክፍል 6.1.4 በመጠቀም በምክክሩ ሂደት የአካል ጉዳተኞችን ክፍት የሥራ ስምሪት ለማሳደግ  እንዲህ ያሉት አካላት ልምድና አውቀት እንዴት በበለጠ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ለማስረዳት የገለጻ ማሳያ 108ን ይጠቀሙ፡፡ አንዳንድ ልዩ አገልግሎት ሰጪዎች ብዙ አካል ጉዳተኞች ወደ ክፍቱ የሥራ ስምሪት ገበያ ለመግባት ከቻሉ ለአገልግሎቶቻቸው የሚኖረው ፍላጎት ስለሚቀንስ ራሳቸውን ለማስማማትና ለመለወጥ እንደሚገደዱ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ አንዳንድ ልዩ አገልግሎት ሰጪዎች ለምሳሌ በሥራ ምደባ ዘዴዎች ወይም በሥራ ስምሪት ላይ እያሉ ድጋፍ በመስጠት አማካይነት አስቀድመው በክፍቱ የሥራ ገበያ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት በንቃት እየደገፉ ይሆናል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የትኛው ዘዴ እንደሚሠራና የትኛው ዘዴ የማይሠራ በመሆኑ ዙሪያ ዋጋ ያለው ምክር ለመስጠት የሚችሉ ሲሆን እንዲሁም ለሌሎች ድርጅቶች እንደ አርአያ በመሆን ያገለግላሉ፡፡

  • ፍላጎቱ ያላቸውን ሌሎች ወገኖች ማማከር
    አስቀድመው ከተጠቀሱት ሌላ በማርቀቁ ሂደት ምክር ቢጠየቁ የሚፈልጉ ሌሎች ባለ ድርሻዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡

    ምክር እንዲጠየቁ የሚፈልጉ ሌሎች ወገኖችን ሃሳብ እንዲያቀርቡ ተሳታፊዎችን ይጠይቁና መልሶቻቸውን በተገላጭ ወረቀቱ ላይ ይመዝግቡ፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል እነዚህ ወገኖች የአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ወላጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም የሚወክሉአቸአውን ማኅበራት፣ ሃይማኖታዊ ተቅዋሞችን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን፣ በአልኮልና አደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት ዙሪያ የሚያተኩሩ ልዩ ድርጅቶችን እንዲሁም እንደ አነስተኛ የንግድ አስተዳደርና የአኮኖሚ ልማት ድርጅቶችን ያካትታሉ፡፡

    ቀደም ብሎ እንደ ተጠቀሰው አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ (በሥራ ስምሪት) ቀጥተኛ ልምድ ሊኖራቸው ከሚችል ፍላጎቱ ካላቸው ወገኖች ጋር ምክክር ለማመቻቸት የሕዝብ አቋም ወረቀቱ ጠቃሚ መሆን እንደሚችል አጽንኦት ይስጡ፡፡ የዐውደ ንባቡን ክፍል 6.1.5 በመጥቀስ በሕግ ማርቀቁ ሂደት ወቅት ምክክርን ለመጠየቅ አንዳንድ ምክሮችን በመዘርዘር ለማጠናቀቅ የገለጻ ማሳያ 109ን ይጠቀሙ፡፡

    • አንድ የአካል ጉዳት ሕግ ወይም ፖሊሲ በሚጸደቅበት ወይም በሚሻሻልበት ጊዜ ሰፊ ረድፍ ያላቸውን ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም የሚቻሉ የፖሊሲ ሰነዶችና አቀራረቦችን በሚመለከት ሁሉም ዋጋ ያለው ልምድ የሚኖራቸውን ሰዎችና ድርጅቶች፣ በተለይ አካል ጉዳተኞችንና የሚወክአቸውን ድርጅቶች የሠራተኛ ማኅበራትና አሠሪዎችን እንደሚያማክሩ ያረጋግጡ፡፡
    • የኮታ ዘዴዎችን በማስተዳደርና የመድልዎ አልባነት ሕግን በመቆጣጠር የተሳተፉት አካላት እንደ ቻሉት ሁሉ ነፃ ባለሙያ አማካሪዎች ደግሞ የሚጫወቱት ሚና ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ያጋጠሙ ችግሮች ሊታወቁና በበቂ ሁኔታ መልስ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
    • የሕግ ወይም የፖሊሲ እርምጃዎች በሚረቀቁበት ወይም በሚሻሻሉበት ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን ማሳተፍና ማማከር፣ የእነዚህም ሰዎች ልምድና እውቀት ሙሉ በሙሉ እንደ ተዳሰሰ ለማረጋገጥ አማራጭ ዘዴዎችን ወይም መግባቢያን ማጤን ይጠይቃል፡፡
    • የመንግሥት ባለሥልጣኖች ተገቢ የሕግና የፖሊሲ እርምጃዎችን ለመፍጠር እንዲረዳቸው የማኅበራዊ አጋሮችን ልምድና አርቆ አስተዋይነት ለመጠቀም መጣር ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ለአንድ ኮታ ስላለው ፍላጎትና ኮታው መያዝ የሚኖርበትን መልክ ተጨባጭ ዳሰሳ በማካሄድ፣ ወይም መድልዎ አልባ እርምጃዎችን በመፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡