የሥልጠና ዝርዝር
4.4 መደበኛ ገለጻ - ኮታው በተግባር እንዲሠራ ማድረግ
-
ዒላማ በሆነው የተጠቃሚዎች ወገን (አካል ጉዳተኞች) እና ግዴታዎች በተጣሉበት ወገን (አሠሪዎች) መጠንና ባህርይ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ሕግና ፖሊሲ አውጪዎችን የሚያስችሉ እስከ ሆኑ ድረስ የኮታ አሠራሮች ለብሔራዊ ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስፈርቶች ተስማሚ መደረግ እንደሚችሉ ለተሳታፊዎች በአጽንኦት ይግለጹ፡፡ አዲስ የኮታ አሠራር በሚመሠረትበት ወይም ነባሩ በሚገመገምበት ጊዜ መጤን የሚኖርባቸውን ጭብጦች Tየገለጻ ማሳያ 71 በመጠቀም ያሳዩ፡፡
ብዙ አገሮች የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ውጤቶች ለማሻሻል የኮታ ወይም የኮታ ቀረጥ አሠራሮችን ቢመርጡም እስካሁን ነፃ ተወዳዳሪነት ያለበትን የአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች የሥራ ስምሪት አንደ ውጤታማ መሣሪያ ወደፊት ለማራመድ በከፊል ብቻ ውጤታማ መሆቸውን ያሉት መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡. ለምሳሌ ለሕጉ ተገዢ ባልሆኑት መቀጫዎች ወይም ቀረጦች የመሳሰሉ ማዕቀቦችን የሚያዝዙ አሠራሮች ባሉአቸው አገሮች ኮታዎች በከፊል ብቻ የተሞሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ማዕቀቦች ለማስፈጸም የኮታዎችና ቀረጦች በበቂ ሰነዶች ሊታጀቡ እንደሚገባ፣ ግን በዚህም ጉዳይ ቢሆን ስኬታማነታቸውን አስመልክቶ ውጤቶች ወሳኝ እንዳይደሉ ጥናት ያመለክታል፡፡
(1) «አካል ጉዳትን ወደ ችሎታ መለወጥ - ለአካል ጉዳተኞች የሥራና የገቢ ዋስትና ለማሳደግ የሚወጡ ፖሊሲዎች» በሚል ርእስ በኤኮኖሚያዊ ትብብርና የልማት ድርጅት በ20 አገሮች በተካሄደ ጥናት ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት አገሮች የግዴታ ኮታ አሠራሮችን እንደ ተጠቀሙ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ በአሠሪዎች ላይ የተጣሉት ግዴታዎች በኢጣልያ 7 ከመቶ፣ በፈረንሳይና በፖላንድ 6 ከመቶ፣ በጀርመን 5 ከመቶ፣ በኦስትሪያ 4 ከመቶ፣ በቱርክ 4 ከመቶ፣ እንዲሁም በኮርያና በስፔይን 2 በመቶ ነበሩ፡፡ ደንቦች አነስተኛ የሠራተኞች ብዛት ላሉአቸው አሠሪዎች ብቻ ያገለግሉ ነበር፤ ይህም በኮርያ የሚጠይቀው 300፣ 50 በስፔይንና በቱርክ፣ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ከ15 እስከ 25 ነው፡፡ እንዳንድ አገሮች ጽኑ አካል ጉዳት ያለባቸውን በኮታው ዓላማዎች ለማካተት ብለው በሁለት ወይም በሦስት እጥፍ እንዲቆጠሩ ያዝዛሉ፡፡ አቀራረቡ በመብት ላይ የተመሠረተ (ፀረ መድልዎ)፣ በግዴታ ላይ የተመሠረተ (ኮታ) ይሁን ወይም በማትጊያዎች ላይ የተመሠረተ (ፈቃደኛ) በዋነኛነት ጥበቃ የሚያገኙት በወቅቱ አሰናካይ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሠራተኞች እንደ ሆኑ ጥናቱ ደምድሞአል፡፡ አንድ አካል ጉዳተኛ አመልካች እንዲቀጠር የኮታ ዘዴዎች አነስተኛ ማትጊያ የሚሰጡ ሆነው ሳለ አካል ጉዳት የሚያጋጥማቸውና ከዚህም የተነሣ በኮታ የመቆጠር መብት ያላቸው ሠራተኞች ይዘውት በነበረው የሥራ መደብ የመቆየት ዕድላቸው የበለጠ መሆኑን ተጨማሪ ድምዳሜ ያመለክታል [ገጽ 105]፡፡
(2) በ1976 የጃፓን መንግሥት ኩባኒያዎች የተወሰነ የአካል ጉዳተኞች መቶኛ በሥራ ኃይላቸው ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥን ግዴታ የሚያደርግ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መስፋፋት ሕግ አውጥቶአል፡፡ ሕጉ 56 ወይም ከዚያ በላይ ሠራተኞች ያሉአቸው የግሉ ዘርፍ ኩባኒያዎች ሁሉ ካሉአቸው ቦታዎች 1.8 ከመቶ የሚሆነው በአካል ጉዳተኞች መሞላት እንደሚኖርበት አጥብቆ ያዝዛል፡፡ በመንግሥቱ ዘርፍ፣ በብሔራዊና በከተማ መስተዳድሮች፣ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ድርጅቶች መቶኛው ወደ 2.1 ከመቶ ከፍ ይላል፡፡ ኮታው እንዲታወቅ ከተደረገ ጀምሮ ለሕጉ ያለው ተገዥነት ከሚጠበቀው ያነሰ ሲሆን ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ በጤና፣ ሠራተኛና ደህንነት ሚኒስቴር መግለጫ መሠረት ከሰኔ 2005 ጀምሮ ከግሉ ዘርፍ ኩባኒያዎች 42.1 ከመቶው፣ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ድርጅቶች አንዲሁም ብሔራዊና የከተማ መስተዳድር 44.8 ከመቶው ብቻ ለሕጉ ለመገዛት ተስማምተዋል፡፡ ምንም እንኳ የጃፓን ኮታዎች በኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት አባል አገሮች ያነሱ ቢሆኑም በተጨባጭ የሚታየው ይህ ነው፡፡
(3) 20 ከመቶ ሥራ አጥነት ባለባት ባህሬን መንግሥቱ አንድ ኩባኒያ ሊቀጥራቸው የሚችለውን የውጭ ዜጎች ብዛት ለመገደብ ይሞክራል፡፡ ይሁንና የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ቅጥር ለማበረታታት አሠሪዎች አንድ አካል ጉዳተኛ ሠራተኛ በቀጠሩ መጠን ሁለት የውጭ ዜጎች እንዲቀጥሩ መንግሥቱ ይፈቅዳል፡፡»
የትኛዎቹ አካል ጉዳተኞች በኮታ ዘዴዎች ዒላማ መሆን ይኖርባቸዋል?
የገለጻ ማሳያ 72ን በመጠቀምና የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.1 በመጥቀስ አካል ጉዳተኞች በሕዝቡ ውስጥ ሰፊና የተሰባጠረ ክፍል እንደሚይዙ፣ እንዲሁም በጣም የተለያዩ ችሎታዎችና እክሎች ያሉባቸውን ሰዎች እንደሚያካትቱ ያስረዱ፡፡
ይህን በማወቅ አንዳንድ የኮታ ዘዴዎች ሁሉንም አካል ጉዳተኞች ዒላማ ሲያደርጉ ሌሎቹ ደግሞ ጽኑ አካል ጉዳት ያለባቸውን ዒላማ ያደርጋሉ፡፡ የኋለኛው ቡድን ከአካል ጉዳት የመድልዎ አልባነት ሕግ መኖር በጥቂቱ ለመጠቀም የሚችል፣ በመድልዎ አልባ አካባቢዎችም ቢሆን ለመወዳደርና በግል መልካም ችሎታዎቻቸው የሥራ መደቦችን የማያሸንፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ በአጽንኦት ያስቀምጡ፡፡ ስለዚህ በኮታ መልክ የታቀደ የአዎንታዊ ተግባር እርምጃ ለዚህ ቡድን የሥራ ስምሪትን ለማሳደግ ተገቢ መሣሪያ ሊሆን ይችላል፡፡«በጀርመን የኮታ ዘዴው ጽኑ አካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች በተለይ የታቀደ ነው፡፡»
«በኔዘርላንድስ የአሠራሩ ዋነኛ ዓላማ የአቤቱታ አቅራቢዎችን ብዛት ለመቀነስ በመሆኑ የፈቃደኛ ኮታ አሠራር የአካል ጉዳት ጥቅም ለማግኘት መብት ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ሸፍኖአል፡፡ ምንም እንኳ ፈቃደኛ ኮታው በሥራ ላይ ባይኖርም አሁንም ቢሆን ከሠራተኞቻቸው አምስት ከመቶ የአካል ጉዳት የሥራ ስምሪት ያላቸው አሠሪዎች ከማኅበራዊ ዋስትና ግብሮች ነፃ ለመሆን ብቁ ናቸው፡፡»ሁሉንም አካል ጉዳተኞች ከሚሸፍነው ዓለም አቀፍ የኮታ ዘዴ ጋር የሚያያዙ መለያዎችና ኃላፊነቶችን ጮኽ ብለው እንዲዘረዝሩ ተሳታፊዎችን ይጠይቁ፡፡ አዎንታዊ መለያዎቹ (1) የኮታ ዘዴዎች የማኅበራዊ ደህንነት ጥቅሞች የሚያገኙ ሰዎች ብዛት መቀነስን የመሳሰሉ ይበልጥ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዒላማ ለማድረግ ይረዳሉ፣ እንዲሁም (2) እጅግ ዝግጁ የሆኑትን የሥራ ቦታ በማግኘት ዕድል እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡ ኃላፊነቶቹ፡- (1) አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ብቻ መካተታቸውን፣ እና (2) እጅግ ጽኑ አካል ጉዳት ያባቸው ግለሰቦች ሥራ አጥ ሆነው ወይም በዝቅተኛ ሥራ ተሰማርተው መኖር የሚቀጥሉ መሆናቸውን ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡ የትኛውም አቀራረብ ቢወሰድ ለታሰበው ወይም ለታቀደው ውጤት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት በመግለጽ ይደምድሙ፡፡
- በኮታ መሠረት ለሥራ ስምሪት ብቁ የሆኑት እንዴት መለየት ይቻላል?
የገለጻ ማሳያ 73ን በመጠቀምና የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.2 በመጥቀስ ኮታው ውጤታማ እንዲሆን በኮታው መሠረት ለሥራ ስምሪት ብቁ የሆኑትን ለመለየት ሁለት እርምጃዎችን ማካተት እንዳለበት ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ እነዚህ እርምጃዎች በግለሰቡ ውሱን የመሥራት አቅምና እንዲህ ያሉት ሰዎች በአስተዳደራዊ መንገድ ተለይተው በሚታወቁበት ሁኔታ ዙሪያ የሚያተኩር የአካል ጉዳት ትርጓሜን ያካትታሉ፡፡
አንድ የኮታ ዘዴ በሚቀረጽበት ጊዜ በጣም ትክክለኛዎቹ ጥቅሞች በዚህ አሠራር አካል ጉዳት እንዳለባቸው ለተመዘገቡት ወይም «ለታወቁት» እንደሚጨምሩ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ለቀረጻ የሚሰጠው ግምት እንደ ማግለል፣ ወይም በችሎታ እጥረቶች ዙሪያ ትኩረትን ማድረግ ከመሳሰሉ ከምዝገባ ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ችግሮች በመቀነስ ረገድ ይረዳል፡፡ ይህን ግብ የማሳኪያ አንዱ መንገድ ምዝገባ አንድን ግለሰብ በኮታ አሠራር እንዲሸፈን ብቻ ሳይሆን ተያያዥ ለሆኑ ጥቅሞች፣ የሥራ ስምሪት በማግኘት እና/ወይም ይዞ በማቆየት ረገድ ለመርዳት ለሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ብቁ እንደሚያደርገው ማረጋገጥ ነው፡፡ አካል ጉዳት ለኮታ ዘዴ ዓላማዎች የሚተረጐምበት መንገድ ለማኅበራዊ ዋስትና ከሚያገለግለው ትርጓሜ የተለየ እንደ ሆነ እባክዎ ለተሳታፊዎቹ ያሳስቡ፡፡ለኮታው ብቁ የሆኑትን የመለያ ዘዴ በሚፈጠርበት ጊዜ ግምት ሊሰጣቸው የሚገቡትን የተለዩ ጉዳዮች አጉልተው ያሳዩ፡፡ በውሱን የሥራ አቅም ዙሪያ ከመሆኑ ይልቅ የአካል ጉዳት ትርጓሜው በእክል ላይ የሚያተኩር ከሆነ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በትክክል የሚጠቀሙት ኮታው ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ዝቅተኛ የመሥራት አቅም ያላቸው ግለሰቦች እንደ ሆኑ ለማረጋገጥ ይህን ማስወገዱ አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም ለመሥራት ባለመቻልና በውሱን የመሥራት አቅሞች ላይ ማተኮር ካለባቸው ለኮታው የሚደረገው የምዝገባ ሂደት ግለሰቦችን በአሉታዊ መልኩ ሊነካ ይችላል፡፡ ስለዚህ ግለሰቦቹን ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎችን ለመቀነስና ክብር እንዲሰማቸው ለማድረግ በኮታ ምዝገባ አሠራሩ ውስጥ ማትጊያዎች እንዲገቡ መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ለኮታው ብቁ ከመሆን ጥቅም ይልቅ አካል ጉዳትን ለማረጋገጥ የህክምና ምርመራ የሚጠይቁ አካላዊና ስሜታዊ ወጪዎች ለግለሰቡ በጣም ውድ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ኮታው የተወሰኑ አካል ጉዳተኞችን በተለይ መጥቀም ይኖርበታልን? የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.3 በመጥቀስ አንድ ኮታ ጽኑ አካል ጉዳት ላለባቸው ወይም አካል ጉዳት ነክ ጥቅም ለሚጠይቁት የታቀደ ቢሆንም አሁንም የሥራ ስምሪት በማግኘት ረገድ የተለየ ችግር የሚያጋጥማቸው አለዚያም የሥራ ስምሪታቸው በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት ማደግ የሚኖርበት ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለተሳታፊዎች ያሳስቡ፡፡ ሰዎቹ እነማንን ሊያካትቱ እንደሚችሉ ለማሳየት የገለጻ ማሳያ 74ን ይጠቀሙ፡- በተለየ ሁኔታ ጽኑ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች፤ ከጦርነት ተመላሽ አካል ጉዳተኞች፤ የሥልጠና ወይም የለማጅ ቦታዎችን የያዙ አካል ጉዳተኞች፣ ሁለተኛ ደረጃ መድልዎ የሚያጋጥማቸው አካል ጉዳተኞች (ለምሳሌ ሴቶች፣ አረጋውያን ሰዎች፣ እንዲሁም በጐሣዊ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖታዊ፣ ወይም በፆታዊ ዝንባሌ በአናሳ ወገኖች ውስጥ የሚፈረጁ ሰዎች)፡፡
የኮታ አሠራሮች በአካል ጉዳት ማኅበረሰብ ውስጥ ዒላማ የሆኑትን ወገኖች እንዲቀጥሩ ለአሠሪዎች ተጨማሪ ማትጊያዎች ለመስጠት ማገልገል እንደሚችሉ በዐውደ ንባቡ ገጽ 40 የቀረቡትን የጀርመንና የፈረንሳይ ምሳሌዎች በመጥቀስ ያስረዱ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ዒላማ በሆኑት ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ከአንድ በላይ የኮታ መደብ እንደ ያዙ ይቆጠራሉ - ስለዚህ ይህንን የኮታ ግዴታቸውን እንዲያሟሉ ለአሠሪዎች የቀለለ ያደርገዋል፡፡
«በፈረንሳይና በጀርመን የሥልጠና ወይም የተለማማጅነት ቦታ የሚይዘው አካል ጉዳተኛ ግለሰብና በተለየ ሁኔታ ጽኑ አካል ጉዳት ያለበት ግለሰብ ሁለት ወይም ሦስት የኮታ ቦታዎችን እንደ ያዙ መቆጠር
ይችላሉ፡፡»ወጥ ኮታ ወይስ የተለያዩ የኮታ መጠኖች?
የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.4 በመጥቀስ አንድ መንግሥት ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ወይም ለአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተለያዩ የኮታ ዒላማዎች በማስቀመጥ ተቃራኒ አንድ ብቻ የኮታ ዒላማ (ለምሳሌ፣ ከሥራ ኃይሉ ከሦስት እስከ አምስት ከመቶ) ለመምረጥ ለምን እንደሚፈልግ ተሳታፊዎችን ይጠይቁ፡፡ የቡድኑን መልሶች በፍሊፕቻርት ወረቀቱ ላይ ይመዝግቡ፡፡አንዳንድ ክፍሎች ወይም ክልሎች ለአካል ጉዳተኞች አመቺ የሆኑ ሰፋ ያሉ የሥራ መደቦችን ሊሰጡ ስለሚችሉ፤ ወይም አንዳንድ ክፍሎች ወይም ክልሎች ጽኑ አካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች አመቺ የሆኑ ውሱን ብዛት ያላቸውን የሥራ መደቦች ብቻ ሊሰጡ ስለሚችሉ ዒላማ የሆኑ ኮታዎች ሊገለግሉ እንደሚችሉ በማስረዳት የገለጻ ማሳያ 75ን ተጠቅመው የቡድኖቹን መልሶች ያጠናክሩ፡፡
የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች አንፃራዊ መጠን ከአገር አገር፣ ወይም ከክልል ክልል ስለሚለያይ እነዚህ ጭብጦች አግባብነት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስረዱ፡፡ እያንዳንዱ ጭብጥ የተለያዩ አካል ጉዳቶች ያሉአቸውን ሰዎች ለመቅጠር የተለያዩ አጋጣሚዎች ይሰጣል፡፡ በእነዚህም ዘርፎች ውስጥ ቢሆን በጥቅም ላይ ባሉት የምርት ሂደቶች የሚወሰኑ ልዩነቶች አሉ፡፡ በውጤቱም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጠቃሚ ሚና ከሚጫወቱበት የሥራ ስምሪት ጋር ሲነጻጸር በተጠናከረ የሥራ ኃይል የሚጠቀም የሥራ ስምሪት አንዳንድ የአካል ጉዳት ዓይነቶች ላሉባቸው ሰዎች ፈጽመው የተለዩ የውህደት አጋጣሚዎችን ይሰጣል፡፡
«በ1953 ተቋቁሞ ለአሁኑ የኮታ አሠራር መንገድ ጠራጊ በሆነችው በጀርመን ለመንግሥቱ ዘርፍ እንዲሁም ለባንክና ለኢንሹራንስ ዘርፎች የ10 ከመቶ ኮታ፣ ለተቀረው የግሉ ዘርፍ 6 ከመቶ ኮታ በጀማሪ ደረጃ ተቀምጦአል፡፡»
«በኔዘርላንድስ ከወዛደር አምራቾች ይልቅ በአብዛኛው ቁጭ ብሎ የሚከናወን ሥራ ያላቸው የቢሮ ሠራተኞች ከፍተኛ ኮታ እንዲኖራቸው አሁን የሌለው የኮታ አሠራር ለተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ መጠኖችን ተጠቅሞአል፡፡»
«በቻይና የኮታው የተወሰነ ደረጃ በማእከላዊው መንግሥት ስር በክፍለ ሀገራት፣ በራስ ገዝ ክልሎች በከተሞች ይወሰናል፡፡ ከጠቅላላ ሠራተኞች የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞች መቶኛ ቢያንስ 1.5 መሆን አለበት፡፡»ሁሉንም አሠሪዎች የሚሸፍን የኮታ ዕቅድ ከማጽደቅ አስቀድሞ አለዚያም የተለያዩ ዘርፎችን ወይም ክልሎችን ዒላማ የሚያደርግ ልዩ ኮታ ማስቀመጥ ያስፈልግ እንደ ሆነ ከመወሰኑ በፊት በአንድ አገር ውስጥ የሚደረግ አጠቃላይ የሥራ ስምሪት ዘርፎች ክለሳ መካሄድ እንደሚኖርበት በመግለጽ ይደምድሙ፡፡
- ተገቢው የኮታ መቶኛ ምንድር ነው?
ተገቢውን የኮታ መቶኛ መወሰን አንድ ሰው ሊያስበው እንደሚችለው የተወሳሰበ አይደለም፡፡ Tየገለጻ ማሳያ 76ን በመጠቀምና የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.5ን በመጥቀስ የኮታ መቶኛ ለሥራ ፈቃደኛና ዝግጁ በሆኑት አካል ጉዳተኞች ብዛት፣ እንዲሁም በኤኮኖሚው ውስጥ ባሉ ኩባኒያዎች መጠን አጭር ታሪክ በመመልከት ዙሪያ የተመረኮዘ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ አገሮች በዘርፉ ላይ በመመርኮዝ የሚለያዩ የኮታ ግዴታዎች እንዳሉአቸው ለተሳታፊዎች ያስረዱ፤ ይኸውም እንደ ማምረቻ ላሉ ይበልጥ የተጠናከረ የሥራ ኃይል ላላቸው ዘርፎች ዝቅተኛ መስፈርቶች እንዲሁም የጽህፈት ሥራ ለመሰሉ ቁጭ ብለው የሚሠሩ የቢሮ ሥራዎች ከፍተኛ ኮታዎች ማለት ነው፡፡«በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ የኮታ መቶኛ በስፔይን ባለው 2 ከመቶና እንዲሁም ኮታው አካል ጉዳተኞችን ብቻ ሳይሆን ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፣ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕፃናትና ስደተኞችን ደግሞ በሚያካተቱባት ኢጣልያ 15 ከመቶ መካከል ይለያያል፡፡»
የተለዩ የአካል ጉዳት ዓይነቶች ወይም ደረጃዎች ላሉባቸው ሰዎች ልዩ እርዳታ ያስፈልጋቸው እንደ ሆነ መወሰን እንደሚኖርበት ደግሞ አጽንኦት ይስጡ፡፡ ይህ መረጃ አሠሪዎች ሁሉ የኮታ ግዴታቸውን ቢያሟሉ ሊገኝ በሚችለው የሥራ መደቦች ብዛትና የሥራ መደብ መስፈርቶችን ማሟላት በሚችሉ አካል ጉዳተኛ ሥራ ፈላጊዎች ብዛት መካከል ንጽጽር ለማድረግ ያስችላል፡፡
- አነስተኛና መካከለኛ መጠን ያላቸው አሠሪዎች መካተት ይኖርባቸዋልን?
የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.6 በመጠቀስ በተለምዶ አነስተኛና ባለ መካከለኛ መጠን ኩባኒያዎች ከኮታ ግዴታዎች ነፃ ሲሆኑ ይህም በኮታ ዘዴ ውጤታማነት ላይ ተጽእኖ እንዳለው ያስረዱ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከግዴታው ነፃ መሆኑ ከ10 በታች ሠራተኞች ላሉአቸው አሠሪዎች፣ በሌሎች አገሮች ደግሞ ከ300 በታች ሠራተኞች ላሉአቸአው ኩባኒያዎች ያገለግላል፡፡
የገለጻ ማሳያ 77ን በመጠቀም አነስተኛ ኩባኒያዎች በኮታ አሠራር የመሸፈናቸው ወይም ነፃ የመሆናቸው ጥያቄ ለምን የጐላ እንደ ሆነ ያስረዱ፡፡ አዎንታዊና አሉታዊ ዘርፎችን ይግለጹ፡፡
የአነስተኛ ኩባኒያዎችን መካተት የሚደግፉ መከራከሪያዎች አካል ጉዳተኞች በአነስተኛ ኩባያዎች ውስጥ በማኅበራዊ ሁኔታ ቢጠቃለሉ የቀለለ ነው የሚል ሃሳብ በሚያቀርበው ማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ በመጨመር በአንድ አገር ባሉ አነስተኛ ኩባያዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሚቀጠሩበት ጊዜ እንዲህ ያሉት ድርጅቶች መገለል በተመሳሳይ ሁኔታ ሰፊ መጠን ያለው የሥራ ኃይል የሚያገልል ሲሆን በውጤቱም ለአካል ጉዳተኞች የተጠበቁትን ሥራ መደቦች በጐላ ሁኔታ ይገድባል፡፡
የአነስተኛ ኩባኒያዎችን መካተት የሚቃወሙ መከራከሪያዎች አዘውትሮ ኤኮኖሚ ነክ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኮታ አሠራር ስር ድርጅቶች አንድን አካል ጉዳተኛ በሚቀጥሩበት ጊዜ ተጨማሪ ወጪዎች የሚከተሉባቸው ከሆነ፣ እነዚህም ወጪዎች ከብሔራዊ የገንዘብ ተቅዋም ወይም አግባብነት ካለው ድርጅት በሚሰጡ እርዳታዎች የማይካካሱ ከሆነ፣ በአንፃራዊ መልኩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አስተኛ ድርጅቶች ይህን ወጪ ለመሸፈን ያቅታቸውና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሊገኙ ይችላሉ፡፡
«በአውሮፓ ኅብረት በኮታ ሕግ የተሸፈነው የድርጅቶች አነስተኛ መጠን በጀርመን ካለው 20 ሠራተኞች በስፔይንና በቱርክ እስከ 50 ሠራተኞች ይለያያል፡፡ እነዚህ ቁርጥ ያሉ አኃዞች በኮታ አሠራሩ በተሸፈኑት አሠሪዎች ብዛትና በተገኙት የሥራ መደቦች ብዛት ላይ የጐላ ውጤት አላቸው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት ካሉት ኢንተርፕራይዞች ሁሉ ወደ 90 ከመቶ የሚጠጉት ዘጠኝ ወይም ከዚያ ያነሱ ሠራተኞች ያሉአቸው ሲሆን በዚህም በአውሮፓ ኅብረት ካለው የሥራ ስምሪት ወደ 30 ከመቶ የሚጠጋውን የሚፈጥሩ ቢሆንም በማንኛውም የኮታ ዘዴ አይሸፈኑም፡፡ ይሁንና በስፔይንና በፖርቱጋል እንዲህ ባሉት ድርጀቶች ከተቀጠሩት 80 ከመቶ ሠራተኞች በዴንማርክ ካለው 63 ከመቶ ጋር ሲነፃፀር የአነስተኛ ድርጅቶች ብልጫ ከአገር አገር ይለያያል፡፡ ስለዚህ በዴንማርክ ከሚኖረው ይልቅ የአነስተኛ ድርጅቶች ከኮታ ዘዴ መውጣት በስፔይንና በፖርቱጋል እጅግ የላቀ ውጤት አለው፡፡ ኮታው 50ና ከዚያ በላይ ሠራተኞች ላሉአቸው አሠሪዎች በሚያገለግልባቸው እንደ ሞንጎልያ ባሉ አገሮች አነስተኛ አሠሪዎችን ከኮታው ማስወጣት ለአካል ጉዳተኞች ጥቂት የሥራ መደቦችን ያስገኛል፡፡»
አነስተኛ አሠሪዎች በኮታ ዘዴ ማካተት ወይም ማስወጣት ያስፈልግ እንደ ሆነና አንዲሁም በኮታው ለማይሸፈኑ አሠሪዎች የመቋጫ ነጥብ ከመወሰኑ በፊት በአንድ አገር ውስጥ ስላሉ አነስተኛ አሠሪዎች አስፈላጊነት ዳሰሳ መደረግ እንደሚኖርበት ደግመው በመግለጽ ይህን ንኡስ ክፍል ይደምድሙ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ አነስተኛ አሠሪዎች ከፍተኛ የሥራ መደቦች መቶኛ በሚሰጡበት ቦታ እንዲህ ያሉትን አሠሪዎች ከወሰኑ የሚያስወጣቸው ከሆነ የኮታው ውጤት በጐላ ሁኔታ ያነሰ ይሆናል፡
አማራጭ መልመጃ፡- ከላይ ያለውን አማራጭ መልመጃ በመጠቀም ፋንታ በተሳታፊዎቹ መካከል ውይይትን ለማመቻቸት ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች ይጠቀሙ፡፡ ከዚህ በታች ያሉት ጥያቄዎች አንድ ሰው የኮታ አሠራርን ለመጠቀም ወይም ላለመጠቀም በሚያጤንበት ጊዜ መመለስ የሚኖርባቸው የጥያቄ ዓይነቶች እንደ ሆኑ ለተሳታፊዎች ይግለጹ፡፡ የእምቅ መልሶችን ስፋት ለማሳየት ተሳታፊዎች እያንዳንዱን ጥያቄ እንዲመልሱ ይጠይቁአቸው፡፡
- ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ውጤቶችን ለማሻሻል ካለው ግልጽ አጠቃላይ የምኞት ግብ ባሻገር ከኮታ አሠራር አጠቃቀም ምን የተለዩ ግቦች ይጠበቃሉ? ለምሳሌ ኮታዎች የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመፍታት ብቻ የታሰቡ ናቸውን? እንደዚያ ከሆነ ለዚያ ግብ የሚሰጠው ድጋፍ እንዴት ይለካል?
- ዝቅተኛ ክፍያ የሚያስገኙ ሥራዎችን ጨምሮ የአካል ጉዳተኞች ትንሽ የእድገት ዕድል ያለበትን ማንኛውንም ሥራ የማግኘት ግብ እንደ ፖሊሲ ውጤት በበቂ ሁኔታ ተቀባይነት አለውን?
- ባለ መጠለያ ወይም ለብቻው የተነጠለ ሥራ ተቀባይነት ያለው ሥራ ነውን?
- ገንዘብ ሰብስቦ የሙያዊ ተሀድሶና የሥልጠና አገልግሎቶችን ለመርዳት ቀረጦችን የመጠቀም ግብ ተቀባይነት ያለው ውጤት ነውን?
- የእነዚህ የገንዘብ እርዳታዎች አያያዝ እንዴት ቁጥጥር ይደረግበታል፣ ይህንስ ማን ማድረግ ይኖርበታል?
- ከቅጣቶች በተሰበሰቡት እርዳታዎች አጠቃቀም የሚኖረው ግልጽነት እንዴት የተረጋገጠ መሆን ይኖርበታል?
- አሠሪዎች አካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን እንዲቀጥሩና ይዘው እንዲያቆዩ ለማበረታታት ቀረጦች የተሻሉ ዘዴዎች ናቸውን? እርስዎ ስለሌሎች መንገዶች ወይም ጥምር አቀራረቦች ምን ማሰብ ይችላሉ?
- መቀጫዎችን ላለመክፈልና አካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ላለመቅጠር አሠሪዎች ምን መንገዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፣ እርስዎስ እነዚህን አሠራሮች ለማክሸፍ ምን ማድረግ ይችላሉ?
- የአካል ጉዳተኞችን ቅጥርና ሥራን ይዞ መቆየት ከሚነኩ ሌሎች እርምጃዎች ጋር በሚገናኝ መልኩ የኮታ አሠራሮች እንዴት መቀረጽ ይኖርባቸዋል? ለምሳሌ ለአካል ጉዳት ጥቅሞች ብቁነት በሚያገለግሉት ተቃራኒ ብዙ አሠራሮች ለኮታ አሠራሩ የተለዩ አካል ጉዳት ትርጓሜዎችን ይጠቀማሉ - እርስዎ ስለዚህ ምን ያስባሉ?
- በሲቪል መብቶች ላይ የተመሠረተ አቀራረብን ከመሰሉ ሌሎች ማትጊያዎች ጋር በማነጻጸር እርስዎ ስለ ኮታ አሠራሮች ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው? የኮታ አሠራሮች ከነባር የሥራ ሕጎችና ከሠራተኛ ጥበቃ (ሙያ ነክ ደህንነትና ጤና) ሕጎች ጋር እንዲጣጣሙ አንዴት መገንባት ይኖርባቸዋል?
-
ኮታው ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ ማገልገል ይኖርበታልን?
የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.7 በመጠቀስ የመንግሥቱን ዘርፍ አሠሪዎች በኮታ ዘዴ መካተት ወይም መውጣት አለባቸው ከሚሉት አስተሳሰቦች ጋር በሚዛመዱ ድጋፎችና ተቃውሞዎች ዙሪያ ስላሉአቸው ሃሳቦችና አስተያየቶች ተሳታፊዎችን ይጠይቁአቸው፡፡ በብዙ አገሮች የመንግሥቱ ዘርፍ ዋነኛ አሠሪ እስከ ሆነ ድረስ እንደ ሞዴል አሠሪ የሚጫወተው ጠቃሚ ሚና ያለው በመሆኑ ይህንን ዘርፍ ከኮታ ዘዴ ውጭ ማድረግ አፍራሽነት ይመስላል፡፡ ከዚህ ሌላ ሕጉ ለግሉ ዘርፍ ብቻ የሚያገለግል ከሆነ የመንግሥቱ ዘርፍ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ቁርጠኛ የመሆኑን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ የመንግሥቱ ዘርፍ መልካም አርአያ በማስቀመጥ ረገድ ያለበትን ኃላፊነት በሚመለከት ለተሳታፊዎች መቀመጥ ያለበት አስፈላጊ ነጥብ በተለምዶ መንግሥታት ዋነኛ የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ገዢዎች በመሆናቸው ከዚህም የተነሣ ለእነርሱ አቅራቢዎች በሆኑት ላይ ጫና ለማሳደር በተለየ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ -
ምን አማራጮች ለአሠሪዎች ክፍት መሆን ይርባቸዋል?
ባለፉት ጊዜያት የነበረው የኮታ ቀረጥ ዘዴዎች አሠራር ዒላማ የሆነውን ቡድን ከመቅጠር ይልቅ የኮታ አሠራሩ ግብ በከፊል ብቻ እንዲሳካ በመተው ብዙ አሠሪዎች ለቀረጥ ክፍያው ያላቸውን ዝንባሌ ለተሳታፊዎች በመግለጽ ይህን ሴሚናር ይደምድሙ፡፡ ይህን አዝማሚያ ለመቃወምና አሠሪዎች በበለጠ ንቃት እንዲሳተፉ ለማበረታታት፣ አሠሪዎች የኮታ ግዴታዎቻቸውን እንዲያሟሉ እንደ ሥራ ላይ ሥልጠና አሰጣጥ ወይም አካል ጉዳተኞችን ለሚቀጥሩ የሙያዊ ተሀድሶ ድርጅቶች እንደ ንኡስ ኮንትራት አሰጣጥ ዕድሎች ያሉ ሌሎች አማራጭ መንገዶች መጤን ይኖርባቸዋል፡፡የዐውደ ንባቡን ክፍል 4.4.8 በመጥቀስና የገለጻ ማሳያ 78ን በመጠቀም ሌሎች አማራጮችን ይግለጹ፤ እንዲሁም ኮታዎች ከመሠረቱ ለአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ሥራዎችን ለማሳደግ እንደ ተጀመሩ ልብ እንዲሉ ተሳታፊዎችን በማሳሰብ ይደምድሙ፡፡ በዚህ ክፍል ከተብራሩት ሌሎች የኮታ ዓይነቶች ይልቅ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መስፋፋት የኮታ ቀረጥ አሠራር የላቀ ድርሻ የሚያበረክት ይመስላል፡፡
እርስዎ የኮታ ማስመሰያ እንደሚያካሄዱ ለክፍሉ ይግለጹ፡፡ የመልመጃው ዓላማ ተለይተው የታወቁትን ፍላጎቶች በበለጠ ሁኔታ የሚመጥን የኮታ አሠራርን ፍላጎትና ቀረጻ እንዲገመግሙ፣ እንደምታዎቹንም እንዲያጤኑ፣ ለተሳታፊዎች ዕድሉን ለመስጠት ነው፡፡ ተሳታፊዎቹን ከ5 እስከ 7 ሰዎች በሚይዙ አነስተኛ ቡድኖች ይከፋፍሉአቸው፡፡ በአባሪ «ረ» የቀረበውን መልመጃ ያድሉ፡፡ በአንድ የቅስቀሳ ቡድን ይፋ የሆነ የቅርብ ጊዜ ጥናት የግራ እጅ ተጠቃሚ (ግራኝ) የሆኑ ግለሰቦች ከጠቅላላው ሕዝብ 15 ከመቶውን የሚይዙ ሲሆን ከትምህርታዊ ፐሮግራሞች በፊትና በኋላ በሚሰጥ አገልግሎት ባልተመጣጠነ ሁኔታ ዝቅተኛ ውክልና (ከ3 ከመቶ ያነሰ) ያላቸው ናቸው፡፡ በድኅረ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተቅዋሞች በግራ እጅ ተጠቃሚዎች ላይ የሚፈጸመውን መድልዎ የሚከለክል ሕግ የመቅረጽ ኃላፊነት በተሰጠው የባለሙያዎች ቡድን እርስዎ እንዲገቡ ተጠይቀዋል፡፡ የዚህ ጥረት ክፍል በመሆን በመንግሥት ውስጥ ያለ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የኮታ ዘዴ በሕጉ ውስጥ መጠቃለል ያስፈልገዋል በማለት ቅስቀሳ እያደረገ ነው፡፡ የኮታ አሠራርን መስፋፋት በመደገፍ የእርስዎ ግብረ ኃይል ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች በሚሰጡት መልሶች ዙሪያ መግባባት ላይ እንዲደርስ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ እርስዎ እንዴት ይመልሳሉ?
- መግባባቱ ላይ ለመድረስ ግብረ ኃይሉ የሚፈልገው መረጃ አለ? ከሆነስ ምን ዓይነት ተጨማሪ መረጃዎች ያስፈልጋሉ?
- በተገለጹት ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዞ ምን ዓይነት ኮታ ይመረጣል (የቀረጥ ኮታ፣ ማበረታቻ የሌለው አስገዳጅ ኮታ፣ ወይም አስገዳጅ ያልሆነ ኮታ)?
- የቀረጥ ኮታ ከተመረጠ እርስዎ ዘዴውን እንዴት ያስተዳደሩና ያስፈጽሙታል?
- ማበረታቻ የሌለው አስገዳጅ ኮታ ከሆነ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?
- አስገዳጅ ያልሆነ ኮታ ቢሆን ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?
- የትኛው ዒላማ ቡድን ለኮታው መለየት ይኖርበታል?
- ብቁነትን እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
- ኮታው ከሌሎች ይልቅ ባለ ግራ እጆችን መደገፍ ይኖርበታልን?
- ወጥ ኮታ ወይስ የተለያዩ የኮታ ደረጃዎች ሥራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል?
- ተገቢው የኮታ መቶኛ ምንድር ነው?
- ኮታው በማን ላይ ግዴታ ይሆናል?