የሥልጠና ዝርዝር
4.1 መደበኛ ገለጻ - የኮታ ቀረጥ ዘዴ
-
የኮታ ዘዴዎች በተጠናከረ ማበረታቻ የሚደገፍ አስገዳጅ ኮታ (የኮታ ቀረጥ አሠራር)፣ በውጤታማ ማበረታቻ እና/ወይም በውጤታማ የማጠናከሪያ አሠራር የማይደገፍ አስገዳጅ ኮታ፣ ወይም እንደ መንግሥት መመሪያ ባለ መሪ ሃሳብ ላይ የተመረኮዘ አስገዳጅ ያልሆነ ኮታ በሚባሉ በሦስት መሠረታዊ ክፍሎች እንደሚከፈል ለተሳታፊዎች በማስረዳት ይህን የትምህርት ክፍል ይጀምሩ፡፡ የገለጻ ማሳያ 63ን ተጠቅመው እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ክፍሎች ያስረዱ፡፡ የኮታ ዘዴዎቹ የተናጥል አሰጣጦች ሳይሆኑ ሰፊና ይበልጥ አጠቃላይ የሆነው የመድልዎ አልባነት ሕግ እጅግ አስፈላጊ ፍሬ ነገሮች እንደ ሆኑ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ በኮታ ዘዴዎች ስር አነስተኛ ብዛት ያላቸውን ሰዎች የሚቀጥሩ አሠሪዎች ከሥራ ኃይላቸው የተወሰነው መቶኛ (ኮታ) በአካል ጉዳተኞች መያዙን እንዲያረጋግጡ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ ይህን መሰሎቹ ዘዴዎች መጀመሪያ ብቅ ያሉት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ሲሆን ከወታደራዊ ግዳጅ የተነሣ የአካል ጉዳት የደርሰባቸው የጦርነት ተመላሾች ብቸኞቹ ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ዘዴዎች አነስተኛ አሠሪዎችን በተለምዶ ነፃ አድርገዋል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባለው ጊዜ የኮታ ዘዴዎች ሲቪል አካል ጉዳተኞችን እንዲሸፍኑ የተስፋፉ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ባሉ አገሮች ተቀባይነት አግኘተዋል፡፡ ይሁንና ለአነስተኛ አሠሪዎች የተሰጠው ነፃ የመሆን ዕድል አዘውትሮ ተጠብአቆል፡፡ በጣም በቅርቡ አንዳንድ የኮታ ዘዴዎች ሥነ ኅሊናዊ ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች (በጃፓን እንዳለው የኮታ ዘዴ) እና የአእምሮ ጤና ችግሮች ያለባቸውን ሰዎች (በጀርመን እንዳለው) እንዲያካትቱ ሆነው በግልጽ ተስፋፍተዋል፡፡
በማበረታቻዎች ከማይደገፉ አጠቃላይ የኮታ አሠራሮች እንደ አዎንታዊ ተግባር መታየት ወደሚችሉትና አንዳንዴም ከውጤታማ መድልዎ አልባ ሕግ ጋር ወደሚገናኙት ወደ ዛሬዎቹ የኮታ ቀረጥ አሠራሮች በመሸጋገር የኮታ ዘዴዎች በጊዜ ሂደት ሰፋ ባለ አዝጋሚ ለውጥ ውስጥ አልፈዋል፡፡
ማስታወሻ፡- አንዳንድ አገሮችና በተለይ አንዳንድ የአካል ጉዳት ተሟጋቾች የኮታ ቀረጥ አሠራሮችን ተቃውመዋል፡፡ አንደ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ታላቋ ብሪታኒያና ካናዳ ያሉ አገሮች አብዛኛዎቹ የአካል ጉዳት ማኅበረሰቦቻቸው ኮታዎችን አካል ጉዳተኞች ተገቢ ማመቻቸቶች እስከ ተሰጡአቸው ድረስ አካል ጉዳት እንደሌለባቸው ግለሰቦች በእኩል ደረጃ አምራች ሠራተኞች መሆን ይችላሉ የሚለውን መከራከሪያ የሚያፈርሱ ሆነው ያገኙአቸዋል፡፡ ከቅጣት ለማምለጥ ግለሰቦችን እንዲቀጥሩ ስለሚያስገድዳቸው የኮታ ቀረጥ አሠራር በአሠሪዎች ዘንድ ተቃራኒ አቋም ያመጣል ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህ የኮታ ተቺዎች በቅጣት ከመሆኑ ይልቅ ለማመቻቸቶች እንደ መክፈል ባሉ ማትጊያዎች የበለጠ ጥቅም ይገኛል ብለው ያምናሉ፡፡
- እያንዳንዱን እነዚህን አቀራረቦች ጠለቅ ባለ ዝርዝር እንደሚዳስሱአቸው ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ የገለጻ ማሳያ 64ን በመጠቀም በኮታ ቀረጥ ዘዴ ስር አስገዳጅ ኮታ የተቀመጠ ሲሆን ግዴታቸውን የማያሟሉ የተሸፈኑ አሠሪዎች ሁሉ የማካካሻ ክፍያ እንደሚከፍሉ በማስረዳት ይጀምሩ፡፡ ምንም እንኳ በፈረንሳይ እንዳለው በተለየ ሁኔታ ማኅበራዊ አጋሮች ቢገቡም በዚህ ዓይነቱ የኮታ ዘዴ አማካይነት የተሰበሰበው ገንዘብ አዘውትሮ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ድጋፍ እንዲውል በመንግሥት ባለሥልጣኖች ለሚተዳደር ድርጅት ገቢ ይሆናል፡፡
ከዐውደ ንባቡ ገጽ 33ን በመጥቀስ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይና ከጃፓን የቀረቡትን ምሳሌዎች ያሳዩ፡፡
ጀርመን በ1974 የኮታ ቀረጥ ዘዴን ለመቀበል ከመጀመሪያዎቹ አገሮች መካከል ነበረች፡፡ በ2002 በወጣው ማኅበራዊ ሕግ መጽሐፍ 9 ስር ቢያንስ 20 ሠራተኞችን ያቀፈ የሥራ ኃይል ያላቸው የመንግሥትና የግል አሠሪዎች ከሥራ ኃይላቸው 5 ከመቶው በአካል ጉዳተኞች መያዙን እንዲያረጋግጡ ይጠየቃሉ፡፡ የኮታ ግዴታቸውን የማያሟሉ አሠሪዎች ለማንኛውም ያልተያዘ የኮታ ቦታ የተወሰነ የማካካሻ ቀረጥ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ቀረጡ የአካል ጉደተኞችን የሥራ ስምሪት በተለየ ሁኔታ ለማሳደግ የሚውል ሲሆን ለምሳሌ ከኮታ ግዴታቸው ልቀው ለሚገኙ አሠሪዎች እርዳታ ወይም ሕንፃዎችን እንደ ማስተካከል ወይም የተጨማሪ ሥልጠና አሰጣጥ ያሉ ከአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ጋር ተያያዥ የሆኑ ተጨማሪ ወጪዎች የሚያጋጥሙትን አሠሪ ለመርዳት ሊጠቅም ይችላል፡፡
የኮታ ቀረጥ አሠራር ፈረንሳይን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ደግሞ ተቀባይነት አግኝቶአል፡፡ በፈረንሳይ የኮታ ግዴታውን ካለማሟላት የሚሰበሰቡት ገንዘቦች ለአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ሙያዊ ሥልጠና ድጋፍ ሊውል ይችላል፡፡ በተጨማሪም የፈረንሳይ የኮታ ሕግ ግዴታቸውን በከፊል እንዲያሟሉ ሌሎች አማራጮችን ለአሠሪዎች ይሰጣል፤ ይህም አካል ጉዳተኞችን ከሚያሠሩ ባለ መጠለያ ማምረቻዎች ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በመግዛት፣ ወይም በምልመላ፣ በሥልጠና፣ ሥራን ይዞ በማቆየት ወይም በቴክኖሎጂ ለውጥ ላይ በሚደረግ ማስተካከያ አማካይነት ለአካል ጉዳተኞች ውህደት በማቀድ፣ በአሠሪዎችና በሠራተኞች ማኅበራት መካከል ድርድር የተደረገበትን ስምምነት በመተግበር በመሳሰሉት ነው፡፡
በጃፓን በጠቅላላው የሥራ ገበያ ባለው ቋሚ የሥራ ስምሪትና ሥራ አጥነት ላይ በመመርኮዝ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው የሥራ ስምሪት ኮታ ይለያያል፡፡
-
አንድ አሠሪ የተቀመጠውን ኮታ ማሟላት ሲያቅተው የቀረጥ ክፍያ መስጠቱ ብቻ በቂ እንዳልሆነ አጽንኦት ይስጡ፡፡ ቀረጡ የሚሰበሰብባቸው መንገዶች ደግሞ በቦታው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ሕጋዊ አካላት በአጠቃላይ ገንዘቡን የመሰብሰብና የተሰበሰበውንም የማከፋፈል አስተዳደራዊ ተግባር እንደ ተሰጣቸው ያስረዱ፡፡ የሚከፈለውን ገንዘብ መጠን መገመትና መግለጽ፣ ከዚያም ለዚያ ለተገለጸው ዓላማ ለተቋቋመው ድርጅት ቀረጦቹን የመክፈል ተግባር በዓይነተኛ ሁኔታ ለአሠሪዎች ተሰጥቶአል፡፡ ቀረጦቹ በየዓመቱ፣ በየሦስት ወሩ ወይም በየወሩ የሚሰበሰቡ ወይም የሚከፈሉ ሲሆን አዘውትሮ ወደዚህ ድርጅት በቀጥታ ይዛወራሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች አሠሪዎቹ ቀረጡ እንደሚመለከታቸው ራሳቸውን ለይተው የማያውቁ በመሆኑ ስላሉባቸው የገንዘብ ግዴታዎች በተቆጣጣሪ አካል ይነገራቸዋል፡፡ የገለጻ ማሳያ 65ን ተጠቅመው እንደ ፖላንድ ባሉ አንዳንድ አገሮች ግብር ሰብሳቢዎች የቀረጥ ክፍያዎችን እንደሚሰበስቡና ለተቆጣጣሪ አካላት እንደሚያስተላልፉ በማስረዳት በኦስትሪያና በፈረንሳይ ጥቅም ላይ የዋሉትን አቀራረቦች ያሳዩ፡፡
በኦስትሪያ ብሔራዊ የተሀድሶ ፈንድ አንድ አሠሪ ያለበትን ዕዳ በሚያሰላውና ይህንንም ለአሠሪው በሚያሳውቀው በመንግሥት ሚኒስቴር ይተዳደራል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስለ አሠሪው የኢሹራንስ ግዴታዎች መረጃ የሚያገኝ ሲሆን ይህንን መረጃ የኮታና የቀረጥ ኃላፊነቶችን ለማሰራጨት ይጠቀምበታል፡፡ በፈረንሳይ ፈንዱ AGEFIPH በተባለ ማኅበር የሚመራ ሰሆን በሕግ የተቋቋመው በ1987 ነበር፡፡ የAGEFIPH አስተዳራዊ ምክር ቤት በአሠሪዎችና በሠራተኞች ተወካዮች፣ እንደ ተወካዮች በተመረጡ አካል ጉዳተኞች፣ በማኅበራዊ አጋሮች፣ በአካል ጉዳተኞች ማኅበራትና በሥራ ስምሪትና አንድነት ሚኒስቴር በተመረጡ የሠለጠኑ ሰዎች የተዋቀረ ነው፡፡
በፖላንድ የቀረጥ ክፍያዎች ስለ ግብር ዕዳዎች በሚያዝዘው ሕግ ስር ይመራል፡፡ በዚህ ሕግ ስር የግብር መሥሪያ ቤቶች ክፍያዎችን መቆጣጠርና ለብሔራዊ ተሀድሶ ፈንዱ ተከፋይ መሆን ያለባቸውን ገንዘቦች መሰብሰብ አለባቸው፡፡ አንድ አሠሪ ቀረጡን ለብሔራዊ ተሀድሶ ፈንዱ በቀጥታ መክፈል ቢያቅተው ፈንዱ የፍርድ ቤት ማዘዣ ሳያስፈልገው በቀጥታ ከአሠሪው የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲያወጣ ወይም የአሠሪውን ንብረት እንኳ እንዲወስድ የግብር መሥሪያ ቤቱን መጠየቅ ይችላል፡፡
በቻይና አሠሪዎች ክፍያውን ላዘገዩበት ለእያንዳንዱ ቀን መቀጫ ይከፍላሉ፡፡ -
ያለ ውጤታማ ማበረታቻ አስገዳጅ ወደ ሆኑት ኮታዎች ከማለፍዎ በፊት በአንዳንድ አገሮች ሳይከፈሉ ለዘገዩ የቀረጥ ክፍያዎች አሠሪዎች እንደሚቀጡ ለተሳታፊዎች
ያስረዱ፡፡ በአንዳንድ አገሮች የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ለመደገፍ የገቢ ምንጭ በመፍጠር አቅማቸው ምክንያት የኮታ ቀረጥ ዘዴዎች ከፍተኛ ግምት ይሰጣቸዋል፡፡ ይሁንና አካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ከመቅጠር ይልቅ አሠሪዎች የኮታ ቀረጥ ለመክፈል የሚመርጡ ከሆነ የኮታ ዘዴ አሠራርና ውጠታማነት መልሶ መታየት ይኖርበታል፡፡ ከአካል ጉዳት ጋር ለተያያዙ እንቅስቃሴዎችና አገልግሎቶች የኮታ ቀረጥ ዘዴ እንደ ገንዘብ ምንጭ የሚታይ ከሆነ ሌሎች አቀራረቦች ይበልጥ ገንዘብ ቆጣቢ ስለሚሆኑ መዳሰስ እንደሚኖርባቸው በመግለጽ ይደምድሙ፡፡