የሥልጠና ዝርዝር

አጀማመር፡- ትውውቅ

  • ራስዎን በማስተዋወቅና በአጠቃላይ «እንኳን በደህና መጣችሁ» በማለት ስብሰባውን ይጀምሩ፡፡ መጸዳጃዎችና የእረፍት ቦታዎች የት እንደሚገኙ ይግለጹ፡፡ ሥልጠናውን «ከማጤስ ነፃ» በሆነ አካባቢ የሚያካሄዱ ከሆነ የማጨሻ አካባቢዎች የሚገኙበትን ለተሳታፊዎች ይነገሩ፡፡
  • ማስተማር ከመጀመርዎ አስቀድሞ የኮርሱን አጠቃላይ የመማር ዓላማዎች ለመመልከት ጊዜ ይኑርዎት፡፡ ተሳታፊዎች ስማቸውን፣ ድርጅታቸውን ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲገልጹ፣ በአንድ ዐረፍተ ነገር ማጠቃለያ ምን እንደሚሠሩና ለሴሚናሩ ያላቸውን የተለዩ የመማር ዓላማዎች እንዲያስረዱ ይጠይቁ፡፡ ተሳታፊዎች የተለያዩ የመማር ዓላማዎቻቸውን በሚገልጹበት ወቅት በሴሚናሩ ቆይታ ሁሉ ለማጣቀሻነት እንዲያገለግሉ «የመማር ዓላማዎች» ተብሎ በተሰየመው ፖስተር/ተገላጭ ወረቀት ላይ ይጻፉአቸው፡፡ አንድ የኮርስ ተሳታፊ ከኮርሱ ዓላማዎች ጋር የማይስማማ ልዩ የመማር ዓላማ ለይቶ ሲያመለክት ያ ዓላማ በዚህ ፕሮግራም እንደማይሸፈን ለግለሰቡ መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡ በእረፍት ጊዜ ወይም ከመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ በኋላ ምናልባት ያ ዓላማ መሟላት የሚችልበትን ይበልጥ ትክክለኛ ቦታ ለግለሰቡ ደስ እያለዎት ለመጠቆም ይፈልጉ ይሆናል፡፡
  • ከትውውቆቹ ቀጥሎ ለመማር አካባቢው አንዳንድ መሠረታዊ ደንቦችን ለመመሥረት ጊዜ ይኑርዎት፡፡ «መሠረታዊ ደንቦች» የተሰኘውን የተገላጭ ገጽ በመጠቀም አንዳንድ በደንብ የታወቁ መሠረታዊ ደንቦችን ይጻፉ፤ በምሥጢርነት መጠበቅ፡- በከፍሉ ውስጥ የተባለው በክፍሉ ውስጥ ይቀራል፡፡ ከበሬታ፡- ማንኛውም ሰው ለአመለካከቱ/ለአመለካከቷ እና ለአስተያየቱ/ለአስተያየቷ ባለ መብት ነው/ናት፡፡ ማብራሪያ መጠየቅ፡- ለግል እምነቶች ተቃራኒ ሆነው ለተገለጹ ነገሮች ለክርክር ሳይሆን ለውይይት ዓላማ ጥቄዎችን መጠየቅ ተቀባይነት ያለው ነገር ነው፡፡ አስተማማኝ የመማር አካባቢ ለመመሥረት አስፈላጊ ናቸው ብለው የሚያስቡአቸውን መሠረታዊ ደንቦች እንዲዘረዝሩ ለተሳታፊዎች ዕድል ይስጡአቸው፡፡
  • በሴሚናሩ ሂደት ውስጥ በዚያ የተለየ ወቅት በመሸፈን ላይ ካለው ርእስ ጋር አግባብነት ሊኖራቸው ወይም ላይኖራቸው የሚችል ጥያቄዎች ሊነሡ አንደሚችሉ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፤ ይሁንና ያ አስፈላጊነታቸውን አያሳንስም፡፡ «የማቆሚያ ቦታ–Parking Lot» የተሰኘውን ተገላጭ ገጽ ያቅርቡና በወቅቱ የማይዳሰሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ሲነሡ በዚያ ገጽ ላይ እንደሚጻፉ ያስረዱ፡፡ ጉዳዮቹ ወይም ጥያቄዎቹ ሳይሸፈኑ ከቆዩ በሴሚናሩ መደምደሚያ እንዴት እንደሚፈቱ እና/ወይም የተባሉትን ዓላማዎች ለማሟላት ይበልጥ ተገቢ ወደ ሆነው ቦታ ለማስተላለፍ ጥቆማ በማድረግ ስልቶች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል፡፡
  • ለሥልጠናው ጭብጥ ለማስቀመጥ ለረጅም ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ሥራ አጥነትና በዝቅተኛ ሥራ መሰማራት ምክንያት ራሱ የአካላዊና አእምሮአዊ እክሎች ያሉበት ሰው ነው ተብሎ ይገመት እንደ ነበር ይናገሩ፡፡ አሁን ግን አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች የሚያጋጥሙአቸው አስቸጋሪ ነገሮች፣ ከኅብረተሰቡም መገለላቸው፣ በተለያዩ እክሎቻቸው ምክንያት ሳይሆን ኅብረተሰብ ለዚያ እክል ካለው የአጸፌታ መልስ የተነሣ መሆኑ እንደ ታወቀ ያስረዱ፡፡ ሕጎችና ፖሊሲዎች የዚህ አጸፌታ ክፍል ናቸው፡፡

    በአሁኑ ጊዜ የአካል ጉዳት ጉዳዮች በላቀ ሁኔታ እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እየታዩ ነው፡፡ በሰብአዊ ክብር ላይ የተማከለው የሰብአዊ መብቶች ሕግ መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳብ ሰዎች ሁሉ እኩል መብቶች፣ በተለይ ሕይወትን በሙሉና በምቹ ሁኔታ የመኖር መብት፣ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማንኛውም ሰው ሰብአዊ ፍጡር ነው የሚለውን ቀላል፣ ግን ደግሞ በወሳኝ ሁኔታ አስፈላጊ የሆነውን አስተሳሰብ ያንጸባርቃል፡፡ ለግለሰቦች መብቶች መልስ በመስጠት መንግሥታት ሰብአዊ መብቶችን እንዲጠብቁ፣ እንዲያከብሩና እንዲፈጽሙ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህ ዳግመኛ ግምት በዓለም አቀፍና በብሔራዊ ሕግ ዋነኛ ለውጦችን እያነሣሳ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች በአጠቃላይ፣ እንዲሁም በተለይ በተቀረጹ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች አማካይነት መጠበቅና ማደግ እንዳለባቸው በሰፊው ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ብሔራዊ መንግሥታት ይህንን በሕግ አወጣጣቸው አማካይነት ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡

    በዚህ መመሪያ ውስጥ «ዐውደ-ንባብ» እየተባለ የሚጠቀሰው በሕግ አማካይነት ለአካል ጉዳተኞች እኩል የሥራ ስምሪት ዕድሎችን ማሰከበር፤ መመሪያዎች የተባለው መጽሐፍ የአካል ጉዳትን እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ዳግመኛ ግምት ለማንጸባረቅ በዓለም ሥራ ድርጅት ጽህፈት ቤት የተዘጋጀ መሆኑን ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ እነዚህ መመሪያዎች ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሕግ አርቃቂዎች የታሰቡ ሲሆን የአካል ጉዳተኞችን ሥልጠናና የሥራ ስምሪት በሚመለከት የብሔራዊ ሕጎችን ውጤታማነት በማሻሻል ረገድ ለመርዳት ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህ መስክ የዓሥድ ዓለም አቀፍ የሥራ መስፈርቶችን፣ ነባር የዓሥድ የሥራ ሕግ መመሪያዎችንና እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ የሠራተኛና የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችን በማጣቀስ ተረቅቀዋል፡፡ መመሪያዎቹ ብሔራዊ የእኩል ዕድል ስትራቴጂን ለመገምገም እንዲሁም በብሔራዊ ደረጃ ለሚደረግ ውይይትና ክርክር እንደ መሣሪያ የሚያገለግሉ ሲሆን እንዲሁም ልዩ ብሔራዊ ሕጎች፣ እነዚህንም ሕጎች ለመተግበር የሚወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች እንዴት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችና የሠራተኛ ሕጎች ጋር እንደሚስማሙ ለመለካት እንደ መነሻ ማገልገል ይችላሉ፡፡

የዐውደ ንባቡ ክፍል 2 ከቁልፍ ቃላት አጠቃቀም ጋር ለሕግ አወጣጥ መነሻ የሆኑ መሪ መርሆዎችና ሃሳቦችን ይሸፍናል፡፡ ክፍል 3 እና 4 በነፃው የሥራ ስምሪት ገበያ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ለማሳደግ የሚያገለግሉ ዋነኛ የሕግና የፖሊሲ ዓይነቶችን ሲመረምሩ ክፍል 5 በትግበራ እርምጃዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ክፍል 6 የአካል ጉዳተኞችን እኩል የሥራ ስምሪት ዕድሎችን ለማሳደግ ከሚሹ ሕግና ፖሊሲዎች መጽደቅ ወይም መሻሻል በፊት መቅደም የሚኖርበትን የምክክር ሂደት ይዳስሳል፡፡ ክፍል 7 የአካል ጉዳተኞችን እኩል የሥራ ስምሪት ዕድል የሚያሳድጉ ሕጎችን ተፈጻሚነት ይተነትናል፡፡ የዋነኛ ነጥቦች ማጠቃለያ በክፍል 8 ቀርቦአል፡፡

ዐውደ ንባቡ ለአሠልጣኞችና ለተሳታፊዎች እንደ ተጨማሪ ማስረጃ ከዚህ የትምህርትና የሥልጠና መመሪያ ጋር አብሮ ያገለግላል፡፡