አቀራረብዎን መምረጥ
ይህን መረጃ ለማቅረብ የሚመርጡት አቀራረብና የሚመድቡት የጊዜ መጠን በቀዳሚ ሁኔታ በቡድኑ አወቃቀርና በኮርሱ ተሳታፊዎች የተለያየ ልምድ የሚወሰን ይሆናል፡፡ እነርሱ አንድ ዓይነት ቡድን ናቸው ወይስ የተሰባጠረ ቡድን (ለምሳሌ በተሟጋቾችና በአንጻሩ በፖሊሲ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ግለሰቦች)? ስለ አካል ጉዳትና ስለ እኩል የሥራ ስምሪት ዕድል ጉዳዮች ያላቸው ልምድ ምንድን ነው? ፖሊሲ በማውጣት ረገድ ያላቸው ልምድ ምንድን ነው? የቡድኑ የፆታ፣ የዕድሜና የትምህርት ክፍፍል ምንድን ነው? ለተሳታፊዎች ይበልጥ አግባብነት ያለው አንድ ልዩ ይዘት አለ? የኮርሱን ተሳታፊዎች ብቁ ለማድረግ የሚያስፈልገው አቀራረብና የጊዜ መጠን በሚወሰንበት ጊዜ እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ሌላው በጣም የሚታሰብበት ነገር በኮርሱ ለመሳተፍ ተማሪው የኮሌጅ አለዚያም የዩኒቨርሲቲ ውጤት ያስፈልገው ወይም አያስፈልገው እንደ ሆነ ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ የግንኙነት ሰዓቶች የእርስዎን ተቅዋማዊ ሁኔታዎች የሚወሰኑ ሲሆን ይህን የጊዜ መስፈርት ለማሟላት ልዩ ይዘት ሊስተካከል ይገባል፡፡
ሌላው መደረግ ያለበት ትኩረት የኮርሱን ኅብረተሰብ በሚፈጥሩት ግለሰቦች የሚወከሉት ልዩ ፍላጎቶች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ እያንዳንዱ የኮርስ ተሳታፊዎች እርስዎ ሥልጠናውን በሚቀርጹበት ጊዜ ማጤንና መጠቀም የሚችሉባቸው ምን የተለዩ ጥንካሬዎችና ልምዶችን ወደ መማር አካባቢው ያመጣሉ? ተሳታፊዎች መሟላት ያለባቸው የተለዩ ፍላጎቶች አሉአቸውን? እርስዎ የሰጡአቸውን መረጃ ለመጠቀም ሲሞክሩ ተማሪዎች የሚያጋጥሙአቸው የተለዩ መሰናክሎች ወይም ፈተናዎች ይኖሩ ይሆን? ይህ የመማር ልምዱን በሚቀርጹበት ጊዜ ሊያጤኑት የሚገባ ወሳኝ መረጃ ሲሆን ከተማሪዎች ጋር በመወያየት፣ ካለፉ ትዝብቶች፣ ሰፋ ካሉ ባለ ድርሻዎች ጋር ከሚደረግ ውይይት፣ መረጃዎችና ሪፖርቶችን ከመመርመር፣ ከመደበኛ ፍላጎቶች ዳሰሳ፣ እንዲሁም የኮርስ ተሳታፊዎች ሊሠሩባቸው የሚያስፈልጉ የወቅቱን የሕግ፣ የፖሊሲና የደንብ ሁኔታዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች መሰብሰብ ይኖርበታል፡፡