መቅድም

አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳትና ችሎታ ማስፋፊያ ማእከል መግቢያ ላይ ሆነው ሲጨዋወቱ፡፡

የዓለም ሥራ ድርጅት (ዓሥድ) ለአጋሮቹ በሚሰጠው በዓለም አቀፍ የሥራ ደረጃዎች፣ እውቀትን የማስፋፋት፣ ጥብቅና የመቆምና የቴክኒካዊ ማማከር አገልግሎቶቹ ለአካል ጉዳተኞች እኩል የሥልጠናና የሥራ ስምሪት ዕድሎችን ለማሳደግ ለብዙ አሠርት ዓመቶች ሠርቶአል፡፡ ይህ ሥራ በግንቦት 2008 ወደ ተፈጻሚነት በገባው በተመድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ድንጋጌ አዲስ ጥንካሬ እንዲያገኝ ተደርጎአል፡፡ የዓሥድ የአካል ጉዳተኞች ሙያዊ ተሀድሶና የሥራ ስምሪት ድንጋጌ ቁ. 159 እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሥራ መስፈርቶች ከተመድ ድንጋጌው ጋር በመጣመር የአካል ጉዳትን ጉዳዮች በሰብአዊ መብቶች መዐቀፍ ውስጥ አጥብቀው ያስቀምጡአቸዋል፡፡ እነዚህ ሰነዶች በአንድ ላይ ለዚህ አዲስ የፖሊሲ ራእይ ውጤት ለመስጠት በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች የሚፈለጉትን የሕግና የፖሊሲ የጐሉ ለውጦች ያንጸባርቃሉ፡፡

ይህ የትምህርትና የሥልጠና መመሪያ «በሕግ አማካይነት ለአካል ጉዳተኞች እኩል የሥራ ዕድሎችን ማስከበር» እና ከእርሱ ጋር ተያያዥ የሆነው የሕግ መመሪያ በአየርላንድ መንግሥት በገንዘብ የሚረዳውና «የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት፡ የሕግ ውጤት» የተባለው የዓሥድ ፕሮጀክት አንድ ክፍል ሆነው ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህን መመሪያ በዓለም ዙሪያ ባሉ አገሮች ለአሠልጣኞች እንደ ምንጭ እንዲያገለግል የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ እንዲያዘጋጅ ዓሥድ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ የትምህርትና የሥልጠና መመሪያው በዴብራ ፔሪ (ዓሥድ) እና በአካል ጉዳት ፖሊሲ መፍትሔዎች ተመራማሪ በሆኑት አይሊን ዛይትሰር እርዳታ ከባርባራ መሬይ (ዓሥድ) ጋር በተደረገ የቅርብ ትብብር በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሥራ ስምሪትና አካል ጉዳት ተቅዋም በሚሠሩት በቶማስ ፒ. ጎልደን የተደረሰና የተዘጋጀ ነው፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ይህ የትምህርትና የሥልጠና መመሪያ በመስፍን ከበደ ወደ አማርኛ ተተርጕሞአል፡፡

መመሪያው በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉ የሕግ ፋካልቲዎች እስካሁን ድረስ በአካል ጉዳት ሕግ ዙሪያ ክፍለ ትምህርቶችን ለማስተዋወቅ እንደ መነሻ አገልግሎአል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከአካል ጉዳተኞች ሕጋዊ መብቶች ጋር የተያያዙ የዲግሪ ኮርሶችና ዓመታዊ ዐውደ ጥናቶችን ለአካባቢው አገሮች እንዲሰጥ በዓሥድና በአይሪሽ ኤይድ ድጋፍ በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በ2010 በተቋቋመው የአካል ጉዳት ሕግና ፖሊሲ ማእከል መመሪያው በምንጭነት ያገለግላል፡፡ መመሪያው በዓሥድ ድረ ገጽ www.ilo.org/disability የሚገኝ ሲሆን በዓሥድ ጽህፈት ቤቶች ደግሞ በኅትመት ተዘጋጅቶ ይገኛል፡፡

የተመድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ድንጋጌ በግንቦት 2008 በሕግነት የጸና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሙያዎች መስፋፋትና በሥራ ስምሪት የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በማሳደግ ረገድ አገሮች ከፍተኛ ቅድሚያ እየያዙ ነው፡፡ ለዚህ ነው ይህ የትምህርትና የሥልጠና መመሪያ በጣም ወቅታዊ፣ አካል ጉዳተኞችን ያካተተና ለእነርሱ ተደራሽ የሆነውን የክፍቱን የሥራ ገበያ ራእይ እውን ከማድረግ አኳያ አግባብነት ያለው የሆነው፡፡


ክሪስቲን ኤቫንስ-ክሎክ
ዲሬክተር
የሙያዎችና ተቀጣሪነት መምሪያ

 

ሙሉው እትም በፒ.ዲ.ኤፍ እዚህ ክሊክ በማድረግ ዳውንሎድ ማድረግ ይቻላል፡፡ Achieving_equal_employment_opportunities.zip