የሥልጠና ዝርዝር

7.5 መደበኛ ገለጻ - ሌሎች አቀራረቦች

  • በርከት ባሉ አገሮች የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች ሌሎች የማስፈጸሚያ አቀራረቦችን በመጠቀም የመድልዎና ውክልና የአለመኖር እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሕግ ተፈጻሚነት ጋር የሚዛመዱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደ ሞከሩ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡

    ለምሳሌ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ማላዊና ናሚብያ ባሉ ጥቂት አገሮች የአካል ጉዳት ጉዳዮች በፕሬዚደንቱ ወይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ወዳሉ የሁኔታ ጽህፈት ቤቶች ከፍ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ሁኔታ ጽህፈት ቤት አካል ጉዳተኞችን በኣካታቹ ኅብረተሰብ ውስጥ ለማዋሀድ የሚያለግሉ ወይም የታቀዱ ፕሮግራሞችን ለማስተባበር፣ ለማመቻት፣ ለመቆጣጠርና ለመገምገም የተቋቋመ ክፍል ነው፡፡ ውህደቱን ማስተባበርና ሌሎቹን ተግባሮች ማከናወን የእያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወይም መንግሥታዊ መምሪያ ኃላፊነት በመሆኑ እንዲህ ያሉት ጽህፈት ቤቶች ሚና አገልግሎት አሰጣጥ አይደለም፣ በዚህ ፋንታ አገልግሎቶች በትክክል እንደ ተሰጡ ያረጋግጣሉ፡፡ በአጭሩ ይህ ጽህፈት ቤት ተቆጣጣሪ አካል ነው፡፡ የቀድሞው የሜክሲኮ ፕሬዚደንት ቪንሴንቴ ፎክስ ለአካል ጉዳተኞች ሕዝባዊ ፖሊሲን ለማስተባበር የአካል ጉዳተኞች ውክልናና ማኅበራዊ ውህደት ጽህፈት ቤት አቋቁመዋል፡፡ ያ ጽህፈት ቤት በተራው ማንኛውም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ወይም በእነርሱ ላይ የሚያተኩር አንድ የተለየ ፕሮግራም እንዲያወጣ ጠየቀ፡፡ ደግሞም ጽህፈት ቤቱ የጤና፣ የሠራተኛ፣ የትምህርት፣ የመገናኛዎችና የማኀበራዊ ልማት አምስት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አባላት የሆኑበትን ብሔራዊ የአካል ጉዳት ምክር ቤት ፈጥሮአል፡፡ በማላዊ በፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤት ለአካል ጉዳተኞች ኃላፊ የሆነው ሚንስትር ሥራ የማላዊ አካል ጉዳተኞችን ከፓርላማውና ከካቢኔ ጋር ማገናኘት ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ ፖሊሲዎቻቸው በአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ በሲቪሉ ኅብረተሰብና በመንግሥታዊ ባለሥልጣኖች የሚጻፉ ሲሆን የዚያ ጽህፈት ቤት ሥራ ግን በማንኛውም ፖሊሲ ወይም ለውጥ ዙሪያ በሚሠሩበት ጊዜ የአካል ጉዳተኞችን እይታ እንደሚያጤኑ ማረጋገጥ ነው፡፡ በአጭሩ ይህን አሠራር በሚጠቀሙ አገሮች የአካል ጉዳተኞች ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ወደ ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት ከፍ ማለት ውህደትና ማካተት የሁሉም ሰው ኃላፊነት የመሆናቸውን የተገመተና ተጨባጭ አስፈላጊነት ያጋራል፡፡

    እነርሱ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ለማሳደግና እኩልነትን ለማሳደግ በአሠሪዎች ላይ አዎንታዊ ግዴታዎችን በመጣል አማካይነት ለእነዚህ ጉዳዮች መልስ ሰጥተዋል፡፡

    የእነዚህ አዎንታዊ ግዴታዎች ግብ ብዙ ክፍት የሥራ ስምሪቶች ለአካል ጉዳተኞች (እንዲሁም ለሌሎች ተጎጂዎችና ውክልና ለሌላቸው ወገኖች) መኖራቸውን ለማረጋገጥ ሽፋን የተሰጣቸውን ተቅዋሞች (ለምሳሌ የግል ኩባኒያዎች፣ የመንግሥት ዘርፍ ድርጅቶች፣ ወዘተ.) መልሶ ለማዋቀር እንደ ሆነ ለማስረዳት የገለጻ ማሳያ 127ን ይጠቀሙ፡፡ ስለዚህ ግዴታዎቹ በተለዩ የሥራ ዓይነቶች ወይም በሥልጣን ቦታዎች ያለውን ስር የሰደደ የአካል ጉዳተኞችን ውክልና ማጣት ጨምሮ ከሚታየው መዋቅራዊ መድልዎ አንጻር የተነጣጠሩ ናቸው፡፡ ከአዎንታዊ ግዴታዎቹ የተነሣ ለውጥን ለማምጣት እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ አዎንታዊ ግዴታዎች የተለያዩ መልኮችን የሚይዙ ሲሆን ከእነርሱም አንዱ የውል ተገዢነት እንደ ሆነ ያስረዱ፡፡

  • የውል ተገዢነት
    በውል ተገዢነት ፕሮግራም ስር የመንግሥት ባለሥልጣኖች ተዋዋዮችን ሁሉ፣ ወይም ከመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር መዋዋል የሚፈልጉትን ድርጅቶች ሁሉ፣ የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን (ደግሞም የተጎጂና ውክልና የሌላቸውን ወገኖች) የሥራ ስምሪት በተመለከተ ጥሩ ታሪክ እንዲኖራቸው እንደሚጠይቁ ያስረዱ፡፡ ይህ ተገዢነት ባልተረጋገጠበት ቦታ፣ እነዚህ ተዋዋዮች የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት ለማሳደግ ንቁ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ የዐውደ ንባቡን ክፍል 7.5.1 በመጥቀስ መሟላት ያለበት መስፈርት በአሠሪው ወይም ከላይ ከተጠቀሱት ኮሚሽኖች በአንዱ በሚሰጥ «የምስክር ወረቀት» የሚረጋገጥ ለአካል ጉዳት የሥራ ስምሪት ሕግ ተገዢ ከመሆን ታሪክ ያልበለጠ ሊሆን እንደሚችል ለማስረዳት የገለጻ ማሳያ 128ን ይጠቀሙ፡፡ ይሁንና ማንኛውንም የተገመተ ችግር ለመፍታት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ ወይም እርምጃ መውሰድን ሊያካትት ይችላል፡፡ ለኮታ ዘዴ ተገዢነት ደግሞ መስፈርት መሆን ይችላል፡፡  በውል ተገዢነት ዘዴዎች ስር ያለው ግልጽ ግዴታ መለያየት ይችላል፣ ነገር ግን የመጨረሻ ግቡ በሥራ ኃይል ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ማሳደግና፣ በአንዳንድ ወቅቶችም፣ ክፍያንና ጥቅሞች ማግኘትን እኩል ማድረግ ነው፡፡

    የገለጻ ማሳያ 129ን በመጠቀም በውል ተገዢነት ዘዴ ስር ለአሠሪዎች ሊኖሩ የሚችሉ የልዩ ግዴታዎች ምሳሌዎችን ይግለጹ፡፡

    • የነባር አካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ብዛት መቆጣጠርና ማሳወቅ፡፡
    • የሥራ ስምሪት አሠራሮችን ወቅታዊ ግምገማዎች ማካሄድ፡፡
    • የውክልና አለመኖር በተከሰተበት ቦታ በሥራ ኃይል ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ውክልና ለማሻሻል በአዎንታዊ ተግባር መሰማራት፡፡

    ለውል ተገዢነት ግዴታዎች ተገዢ መሆን ያጋጥመማሉ ተበለው የሚገመቱ አለመጣጣሞችን ለመፍታት የትክክለኛነት ዕቅድ በመውጣት ሂደት ውስጥ የሠራተኛ ማኅበራትን የሚያካትት አሳታፊ አሠራር መሆን እንደሚችል ያስረዱ፡፡ የውል ተገዢነት ግዴታዎችን መደገፍ ሽፋን ያገኙ ድርጅቶችን የሥራ ስምሪት ፖሊሲዎችንና የሥራ ስምሪት መዝገቦች በንቃት በሚመረምር ሕጋዊ አካል ወይም ከላይ ከተገለጹት ኮሚሽኖች በአንዱ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡

    ከዩናይትድ ስቴትስና ከኔዘርላንድስ ተገኝተው በዐውደ ንባቡ ገጾች 74-75 የቀረቡትን ምሳሌዎች በማጠቃለል ይህን ንኡስ ክፍል ይዝጉ፡፡

    የመንግሥት ተዋዋዮች ከሕገ ወጥ መድልዎ እንዲታቀቡ ብቻ ሳይሆን በሥራ ኃይል ውስጥ የዝቅተኞችን ውክልና ለማሳደግ አዎንታዊ እርምጃ እንዲወስዱ በሚጠየቁበት በዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ያሉት አዎንታዊ ግዴታዎች ቀዳሚነትን ይዘዋል፡፡ ከሠራተኛው ሕዝብ 40 ከመቶ የሚሆነውን የሚያሠሩት ወደ 300,000 የሚጠጉ የፌዴራል ተዋዋዮችን እንደሚመለከት የተገመተው ይህ ግዴታ ወደ ምርመራዎችና ክሶች ከሚያመራው የግለሰብ አቤቱታ ይልቅ በአሠሪዎች ላይ ይበልጥ የከበደ ጫና አለው፡፡
    በሰሜን አየርላንድ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ተግባሮቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ የዕድል እኩልነትን ለማሳደግ ተገቢ ትኩረት የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት ባለሥልጣን የዕድል እኩልነትን ለማሳደግ የወጡ ፖሊሲዎች ያስከተሉትን ለውጥ ለመመካከርና ለመገምገም የሚያስችል የባለሥልጣኑን ዝግጅቶች የሚገልጽ፣ እንዲህ ያሉትን ፖሊሲዎች አፍራሽ ውጤት ለመቆጣጠር፣ የግምገማዎቹን ውጤቶች ለማሳተም፣ እንዲሁም ሕዝብ መረጃና አገልግሎቶችን ማግኘቱን ለማረጋገጥ የሚያገለግል የእኩልነት ዕቅድ እንዲያዘጋጅ ይጠየቃል፡፡ እንዲህ ያሉት ዘዴዎች በሰሜን አየርላንድ የእኩልነት ኮሚሽን መጽደቅ ይኖርባቸዋል፡፡

  • የገለጻ ማሳያ 130 የቀረቡትን ዋነኛ ፍሬ ነገሮች በማጠቃለል ደምድሙ

    • በእነዚህ ሕጎች ውስጥ ያለውን ምኞት እውን ለማድረግ የሚሹ የእኩል ዕድሎች ሕግና ፖሊሲዎች ትክክለኛ ትግበራ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ የእኩል ዕድሎች ሕግና ፖሊሲዎችን በሚያጸድቁበት ወይም በሚያሻሽሉበት ጊዜ ሕግና ፖሊሲ አውጪዎች ለእነዚህ መሣሪያዎች ቁጥጥርና ግምገማ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
    • የሕጎችና ፖሊሲዎች ትክክለኛ ቁጥጥርና ትግበራ ይህን እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው ድርጅት ወይም አካል እነዚህን ተግባሮች ለማከናወን አስፈላጊው አቅምና ችሎታዎች እንዲኖረው በቅድሚያ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ችሎታዎች ሕጉ በሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ይቀርቡ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡
    • በፍርድ ቤት ነክ ወይም በሌላ ማስፈጸሚያ መንገድ የሚደረግ የሕጎችና ፖሊሲዎች ተፈጻሚነት የግለሰቦች ብቻ ተግባር አይደለም፡፡ መንግሥትም ደግሞ አስተዳደራዊ ወይም ተቅዋማዊ የማስፈጸሚያ አሠራሮችን የማስተዋወቅ ግዴታ አለበት፡፡
    • አካል ጉዳኞችን የሚመለከቱ ሕጎች በቂና ቀልጣፋ የትግበራና የማስፈጸሚያ አሠራሮች መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እንደ እንባ ጠባቂ ተቅዋም፣ ወይም የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ወይም የእኩልነት ባለሥልጣን ያሉ አስፈጻሚ አካላት እንዲሁም አሠራሮች መጤን ይኖርባቸዋል፡፡