የቃላት መፍቻ

አዎንታዊ እርምጃ፡

ሥርዓተ ፆታን ወይም ወደ ጎን የተገፉ ወገኖችን ይበልጥ የሚወክል እንዲሆን በሥራ ኃይሉ አወቃቀር ውስጥ ያለውን አለመመጣጠን ለማስተካከል በአንድ ኩባኒያ ወይም ተቅዋም የሚወሰድ እርምጃ፡፡

የሠለጠነ ሠራተኛ፡

ከተመጣጣኝ ማመቻቸት ጋር ወይም ይህ በሌለበት ሁኔታ በጥያቄ ውስጥ ያለውን ሥራ እንቅስቃሴዎች ማከናወን የሚችል ሠራተኛ ወይም አመልካች፡፡

ተመጣጣኝ ማመቻቸት፡

ይህ ሕጋዊ ጽንሰ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ እውን የሆነው በአሜሪካውያን አካል ጉዳተኞች ሕግ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በሌሎች አገሮች ሕጎች እንዲሁም በተመድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ድንጋጌ ውስጥ እያገለገለ ነው፡፡ ማመቻቸቱ በእነዚህ የተወሰነ ባይሆንም የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፡- (1) ሠራተኞች የሚጠቀሙባቸውን ነባር ሕንፃዎች ተደራሽና አካል ጉዳተኞች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ማድረግ – ለምሳሌ የሠራተኞች መጸዳጃዎች፤ (2) የሥራ መደብን መልሶ ማዋቀር፣ የሥራ ሰንጠረዦችን መለወጥ፣ ወይም ወደ ክፍት የሥራ መደብ መልሶ መመደብ፤ (3) መሣሪያ ወይም አጋዥ ዕቃዎች ማግኘት ወይም መለወጥ፣ ወይም ፈተናዎችን፣ የሥልጠና ቁሳቁሶችን ወይም ፖሊሲዎችን ማስተካከል ወይም መለወጥ፤ እንዲሁም (4) መስማት ለተሳናቸው ወይም ዝቅተኛ እይታ ላላቸው ሰዎች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች ወይም አንባቢዎች ማቅረብ፡፡

ያልተገባ ችግር (ወይም ሸክም)

ይህ የተመጣጣኝ ማመቻቸት ተቃራኒ ሲሆን በኩባኒያው መጠን፣ ባሉት የገንዘብ ሀብቶችና በተግባሩ ባህርይና አወቃቀር በመሳሰሉት ጭብጦች አኳያ በሚታይበት ጊዜ የጐላ ችግር ወይም ወጪ እንደሚያስከትል ድርጊት ይገለጻል፡፡ ማመቻቸትን ለማድረግ አንድ አሠሪ የምርት መስፈርቶችን ዝቅ ማድረግ አይጠበቅበትም፤ ወይም እንደ ማዳመጫዎችና መነጽሮች ያሉ የግል መጠቀሚያ ዕቃዎችን ለማቅረብ አትገደድም ወይም አይገደድም፡፡