የሥልጠና ዝርዝር

2.6. መደበኛ ገለጻ - በሕግ ውስጥ አካል ጉዳትን መግለጽ

  • የአካል ጉዳት አገላለጽ ማን እንደ አካል ጉዳተኛ እንደሚታወቅ፣ ከዚህም የተነሣ አግባብነት ባለው ሕግ ጥበቃ እንደሚያገኝ የሚወስን መሆኑን ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ ይህ በልዩ ሕግ ወይም ፖሊሲ ክትትል እየተደረገበት ባለው ግብ ላይ እጅግ በጣም የተመረኮዘ ነው፡፡ በሠራተኛ ወይም በማኅበራዊ ሕግ በጠቅላላው ከዳር አስከ ዳር ማገልገል የሚችል ትክክለኛ ወይም አንድ ወጥ የሆነ የአካል ጉዳት አገላለጽ እንደሌለ አጽንኦት ያድርጉ፡፡ አካል ጉዳትን ለመግለጽ አዘውትረው በብሔራዊ ሕግ ውስጥ የሚገኙት ሁለቱን የተለያዩ አቀራረቦች መልሶ ለማየት የገለጻ ማሳያ 26ን ይጠቀሙ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በጠባብ ሊታወቅ ለሚችል ተጠቃሚ ቡድን የታቀደ የቃላት አገባብ፡፡ ዓላማው ለአካል ጉዳተኛ ግለሰቦች ወይም የአካል ጉዳተኞች አሠሪዎች ለሆኑ ግለሰቦች የገንዘብ ወይም የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግ ሕግ ለማርቀቅ ከሆነ ይህ ጥቅም ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡ ድጋፍ እጅግ ለሚያስፈልጋቸው እንደ ታቀደ የሚረጋገጥበት ውሱን፣ ከእክል ጋር ተያያዥ የሆነ የአካል ጉዳት አገላለጽ (የግለሰብ ሞዴል)፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በአካል ጉዳት ላይ ተመሥርቶ ከሚፈጸም መድልዎ ጥበቃ ለማድረግ የታቀደ በስፋት አካታች የሆነ የቃላት አገባብ፡፡ ይህ ጥበቃ የሚደረግለት ቡድን (ማኅበራዊ ሞዴል) የአካል ጉዳት አገላለጽ በጸረ መድልዎ ሕግ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል ይኖርበታል፣ ምክንያቱም አነስተኛ አካል ጉዳት ያለባቸውን፣ ከአካል ጉዳተኞች ጋር የሚዛመዱ ሰዎችንና በስህተት አካል ጉዳት እንዳለባቸው የሚገመቱትን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በአካል ጉዳት ላይ በተመሠረተ መድልዎ መጠቃት ስለሚችሉ ነው፡፡
  • ከአውስትራልያ፣ ከቻይና፣ ከጀርመን፣ ከሕንድ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከታላቋ ብሪታንያ የተገኙ ምሳሌዎች ለተሳታፊዎች ለማሳየት የዐውደ ንባቡን ገጽ 16 ይጥቀሱ፡፡
  • አካል ጉዳትን ለመግለጽ ስለሚያገለግሉት ቃላት ለተሳታፊዎች ለማስረዳት የገለጻ ማሳያ 27ን ይጠቀሙ፡፡ አካል ጉዳተኞችን ለመግለጽ የተለያዩ ቃላት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ «አቅመ ቢሶች»፣ «ስንኩሎች» ወይም «ዘገምተኞች» የተባሉትን የመሳሰሉት ቃላት በብዙዎች ዘንድ የሚያስከፉ ሆነው ሲታዩ የግለሰቡ ማንነት በቀዳሚ ሁኔታ ባለበት እክል ላይ እንደ ተመሠረተ አድርገው ይወስዳሉ፡፡ ሕግ ከሰብአዊ ፍጡራን ክብር ጋር ተስማሚ የሆኑ «አካል ጉዳተኞች» ወይም «አካል ጉዳተኛ ግለሰቦች» የተባሉትን የመሰሉ ቃላት ማካተት ይኖርበታል፡፡
  •  
    አማራጭ መልመጃ፡- የገለጻ ማሳያ 28ን በመጠቀም ግለሰብን የሚያስቀድሙ የቃላት መግለጫ መንገዶችን እንዲለዩ ተሳታፊዎችን በጥንዶች ተከፋፍለው እንዲሠሩ ያድርጉአቸው፡፡ ለመሥራትና ከዚያም መልሶቻቸውን እርስበርስ እንዲጋሩ ወደ 10 ደቂቃ ገደማ ይስጡአቸው፡፡