የሥልጠና ዝርዝር

2.5. መደበኛ ገለጻ - የአካል ጉዳት ጽንሰ ሃሳብ

  • ውጤታማ አካል ጉዳት መድልዎ አልባ ሕግ በሚቀረጽበት ጊዜ ከትላልቁ ፈተናዎች አንዱ አካል ጉዳትን ማብራራት እንደ ሆነ ለተሳታፊዎች ያስረዱ፡፡ አካል ጉዳትን ከማብራራት አስቀድሞ ፖሊሲ አውጪዎች ለማጥፋት የሚሞክሩአቸውን ሁኔታዎች ወይም ለማሳደግ የሚመኙአቸውን ግቦች ማወቅ እንዳለባቸው ያስረዱአቸው፡፡ አካል ጉዳት የሚብራራበትን መንገድ ሊቀይሩ የሚችሉ ሦስት መንገዶች መኖራቸውን እንዲያውቁ ለመርዳት የገለጻ ማሳያ 25ን ይጠቀሙ፡፡
  •  
    አማራጭ መልመጃ፡- በቀድሞ ጊዜ የነበራቸውንና የጠሉትን ከእርሱም የተባረሩበትን ወይም የለቀቁትን ሥራ እንዲያስቡ ተሳታፊዎችን በመጠየቅ ይህን መልመጃ ይጀምሩ፡፡ ተሳታፊዎች ወደ ኮርስ ጓደኞቻቸው መለስ ብለው ሥራውን የለቀቁበት ወይም ለመባረር ያበቃቸው ምክንያት ምን እንደ ነበረ ደቂቃ ወስደው እዲገልጹላቸው ያድርጉአቸው፡፡ ፍሊፕቻርትና መጻፊያ ማርከር በመጠቀም የመልቀቅ ወይም የመባረር ምክንያቶቻቸውን እንዲያጋሩና እንዲመዘግቡ ያድርጉአቸው፡፡ ቀጠሎም ግለሰቦቹ በቀድሞ ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሠሩ - ምንም ያህል ቢሠሩ ሁልጊዜ የሚያቅታቸው፣ እሮሮ የሚያበዙ - ወይም ስኬታማ የሆኑ (አካል ጉዳተኛ የሆኑ ወይም ያልሆኑ) ሰዎችን እንዲያስታውሱ ያድርጉአቸው፡፡ ተሳታፊዎች ወደ ኮርስ ጓደኞቻቸው መለስ ብለው ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሁኔታውን አስቸጋሪ፣ የሚያቅት፣ ወይም የማይሳካ ያደረገባቸው ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለመግለጽ ደቂቃ ይውሰዱ፡፡ ተገላጭ ወረቀትና ማርከር በመጠቀም ተሳታፊዎች አንዳንድ የመልቀቅ ወይም የመባረር ምክንያቶቻቸውን እንዲያጋሩና እንዲመዘግቡ ያድርጉአቸው፡፡. ሁለቱን ዝርዝሮች ጎን ለጎን ይለጥፉአቸውና ተሳታፊዎች አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡባቸው ይጠይቁ፡፡ ስለ ራሳቸው በሚናገሩበት ጊዜ ችግሩን ለአካባቢው እንደሚሰጡ፣ ስለ ሌሎች በሚናገሩበት ጊዜ ግን ችግሩ ሁልጊዜ ከግለሰቡ ጋር የተያያዘ እንደ ሆነ ወዲያውኑ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ አካል ጉዳትን በማብራራት ዙሪያ ቀጣዩን ክፍል ለመጀመር ልዩ ንጽጽር ይሥላል፡፡
  • የህክምና ሞዴልና ማኅበራዊ ሞዴልን በሚመለከት ቀደም ብሎ የተደረገውን ውይይት (ወይም እርስዎ ያንን ከመረጡ አማራጭ መልመጃውን) በመጥቀስ ሁለቱ ተቃራኒ የአካል ጉዳት አመለካከቶች እንዴት ሊለዩ እንደሚችሉ ደግመው ያስረዱ፡፡ የአካል ጉዳትን አጋጣሚ በግለሰቡ ጭብጥ ውስጥ ማስቀመጥ (የህክምና ሞዴል) እንደ ተሀድሶ ህክምና ወይም የማኅበራዊ ደህንነት ሕግ ባሉት መስኮች በተለይ ሊረዳ የሚችል ሆኖ ሳለ የአካል ጉዳትን አጋጣሚ በባህልና በአካባቢ ጭብጥ ውስጥ ማስቀመጥ የመገለል፣ የጉስቅልናና የመድልዎ ስረ መሠረት የሆኑትን መንሥኤዎች በመቅረፍ ረገድ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆን ይችላል፡፡ ማኅበራዊው ሞዴል አንድ ሰው አካል ጉዳት አለበት ተብሎ ይመደብ እንደ ሆነ ለሚቀርበው ጥያቄ መልሱ እንደ ባህል፣ ጊዜና አካባቢ ካሉ ጭብጦች ጋር በመሠረታዊ ሁኔታ የተገናኘ እንደ ሆነ ያውቃል፡፡
  •  
    አማራጭ መልመጃ፡- ተሳታፊዎችን በሦስት አነስተኛ ቡድኖች በመለያየት ይህን መልመጃ ይጀምሩ፡፡ የገለጻ ማሳያ 25ን ተጠቅመው ከታዩት ሦስት ግቦች እያንዳንዱን ለየቡድኑ ይመድቡ፡፡ እያንዳንዱ ቡድን ጊዜ ወስዶ የተመደቡለትን ግቦች እንዲወያይባቸውና የአካል ጉዳቱን የህክምና ሞዴል ወይም ማኅበራዊ ሞዴል ለመጠቀም በተሻለ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን እንዲወስኑ ይጠይቁአቸው፡፡ ጉዳያቸውን በጥልቀት እንዲያሰላስሉ ለእያንዳንዱ ቡድን 20 ደቂቃ ይስጡ፡፡ በዚህ ለመቀጠል እንዲረዳቸው አንድ አወያይና መልሶቻቸውን መዝግቦ የሚይዝ አንድ ጸሀፊ እንዲመድቡ ያድርጉ፡፡ የቡድኑን መልስ ለጠቅላላው ተሳታፊዎች በዝርዝር እንዲያቀርብ ደግሞ እያንዳንዱ ቡድን ዘገባ አቅራቢ መመደብ ይኖርበታል፡፡